7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የሃሳብ ልዕልና፣ ተቋማዊ እመርታ እና የሕዝብ ፅናት የታየበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው- ሳምንታዊ መልዕክት
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን በተሻገረ ተቋማዊ ታሪኳ እና ሀገር በቀል እሴቶቿ የምትታወቅ ጥንታዊት ሀገር ብትሆንም የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግርና የልዩነቶች አፈታት ሂደቷ ግን የነፍጥ ትግልና የኃይል አማራጮች የበዙበት ፈታኝ ጉዞ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በቅርቡ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተጠናቀቀው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይህንን ታሪካዊ ስህተት ያረመና ሀገሪቱ ወደ ሰለጠነ የሀሳብ ፖለቲካ እና ወደ ዘመናዊ የመንግሥት ግንባታ የተሻገረችበትን አዲስ ምዕራፍ በደማቅ ቀለም የጻፈ ሆኗል። ይህ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቀናዒነት በተግባር ያስመሰከረበት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላትና ተቋማት ልዩ ትብብር የታየበት ታሪካዊ ኩነትም ነው።
የዚህ ታሪካዊ ምርጫ ዋነኛ ማሳያ የመራጩ ሕዝብ ንቁና በሳል ተሳትፎ ነው። ክቡር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሊዮኖች በነቂስ ወጥቶ በመመዝገብና በረጅም ሰልፎች ውስጥ በሚደነቅ ትዕግሥትና ስክነት ድምፁን በመስጠት ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በተግባር አሳይቷል። ያለፉትን ታሪካዊ ስህተቶችና ቁጭቶችን እንዳይደገሙ በማድረግ ህዝብ በሃሳብ ልዕልና ብቻ ይበጀኛል የሚለዉን አካል በመምረጥ ሀገራዊ መሻቱንና ብሔራዊ ኩራቱን አረጋግጧል።
ከዚህ በተጨማሪ ይህ ስኬት የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገራዊ ጸጥታና የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ መስዋዕትነትና የተቀናጀ ጥረት ውጤት ነው። የሥልጣን ሽግግርና የፖለቲካ ፉክክር በሰላማዊ መንገድና በምርጫ ብቻ መሆኑን በማሳየት ረገድ የሲቪል ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጫወቱት ሚና የላቀ ነበር። ከዚህም በላይ ከምርጫው ማግስት የምርጫው ባለድርሻ አካላትና ተዋንያን ያሳዩት ሙያዊ ዲስፕሊን እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አዲስና ስልጡን የፖለቲካ ባህል መፈጠሩን አስመስክሯል፡፡
የምርጫውን ስኬታማነት ተከትሎ ለተሳተፉ አካላት የተሰጠው ሀገርአቀፍ ዕውቅና፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥርዓት የሚያዘምንና ተቋማዊ እመርታን የሚያሳይ መሆኑ በሰፊው ተመስክሮለታል። ክቡር የፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ይህንን አዲስ ምዕራፍ ሲያብራሩ፤ "ሀገራዊ ተቋማት በብዙ ጥረትና በጋራ መስዋዕትነት የተመዘገቡ ሀገራዊ ድሎችን እውቅና የመስጠት ልምድ ማዳበራቸው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ ይህ ሊለመድ፣ ሊሰርፅና ሊቀጥል የሚገባው የፖለቲካ ሥርዓትን የሚያዘምን አሰራር ነው" ብለዋል።
ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ ምርጫው በተካሄደበት ዕለት እና አሁን በድህረ-ምርጫ ምዕራፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ሆነው መፈጸማቸው ኢትዮጵያ ለሰለጠነ የሀሳብ ፖለቲካ ያላትን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳየችበት ታላቅ ክስተት ነው። በሕዝቡ ፅናት፣ በባለድርሻ አካላት ቅንጅትና በተቋማት ጥንካሬ የተመዘገበው ይኸው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድል የኢትዮጵያን ተስፋ ይበልጥ የሚያለመልም እና ለቀጣዩ ትውልድ አስተማማኝና የበለፀገች አገር የማስረከብ ራዕይን ለማሳካት ፅኑ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡
ኢትዮጵያ መርጣለች፤ አሸንፋለችም!
ብልፅግና ፓርቲ
ሰኔ 08፤ 2018 ዓ/ም