"ሰላም ሲኖር ሴቶች ይበረታሉ፣ ሴቶች ሲበረቱ ደግሞ ሀገር ትጸናለች"- ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ
በ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለክልልና ለፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሴቶችን ከህዝቡ የማስተዋወቅ ክልላዊ መድረክ በሆሳዕና ከተማ በታላቅ ድምቀት ተካሄደ።
በመድረኩ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ፋጤ ሰርሞሎ፣በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣የክልሉ ሴቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሽመልስ፣ሴት ዕጩዎች፣የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ ሴቶች የቤተሰብ መሰረት፣ የማህበረሰብ አምድ እና የሀገር እድገት ሃይልና ተስፋ ናቸው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን የኢኮኖሚ ነፃነት ለማረጋገጥ
፣ የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ፣ የንግድ ድጋፍንና የብድር አገልግሎትን ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሴት ልጆች በትምህርት እንዲበረቱ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ የፓርቲው የነገ የሀገር ግንባታ አጀንዳ ስለመሆኑም ዶክተር ዲላሞ አብራርተዋል።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውንም አይነት ጥቃቶች፣ አድሎዎችና በደሎች ፓርቲው በጽኑ እንደሚታገላቸውም
አስገንዝበዋል።
"ሰላም ሲኖር ሴቶች ይበረታሉ፣ ሴቶች ሲበረቱ ደግሞ ሀገር ትጸናለች" ያሉት ዶክተር ዲላሞ፣ መላው የክልሉ ሴቶች በግንቦት 24 በሚካሄደው ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለብልጽግና ፓርቲ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሽመልስ በበኩላቸው፣ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች መስራቱን ገልጸዋል።
በክልሉ የሴቶች የአመራር ሰጪነት እያደገ መምጣቱንም አንስተው፣ሴቶችን ለማብቃትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ፓርቲው በተለየ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
በሴቶች ክንፍ አባላት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ያነሱት ወይዘሮ ኤልሳቤት፣7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የግንቦቱ ምርጫ ለሴቶች ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑንም ወይዘሮ ኤልሳቤት ጠቁመው፣የክልሉ ሴቶች እህትማማችነትና ወንድማማችነትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ብልጽግና ዕውን መሆን መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።