Prosperity Party

"የፓርቲያችንን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር አፈጻጸምን ከብዛት ወደ ጥራት ማሸጋገር ተችሏል" - አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት የተከናወኑ የፓርቲ ሥራዎች ላይ ከዋና ጽ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ እና ሌሎች የዋና ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ  በመድረኩ እንደገለፁት ባለፉት ወራት በተሰሩ ጠንካራ ስራዎች የፖርቲያችንን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር  ከብዛት ወደ ጥራት ማሸጋገር መቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህም ምክንያት የሆኑት በተለያዩ ጊዜያት ለ14.7 ሚሊዮን አመራሮችና አባለት የተሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ተከታታይነት ያለዉ የዉይይት መድረኮች፣ ምዘና በወቅቱ መካሄዱና አደረጃጀቶችን የማጥራት  ሰፊ ስራ በመከናወኑ ነዉ ብለዋል።

በንቅናቄ ሲሰሩ የነበሩት የፓርቲያችን የልማት ኢኒሼቲቮች፥ የሌማት ትሩፋት፣ አርንጓዴ አሻራ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ዉድነት ለማቃለል፣ የበጋ ስንዴ፣ ከተረጂነት ለመዉጣትና የመሳሰሉት በፓርቲና መንግስት መዋቅር ቅንጅት በልዩ ትኩረት በመሰራቱ አፈፃፀማቸው በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ባለፉት ወራት በመላዉ ሀገሪቱ ከ11.8 ሚሊዮን በላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ አካለት ጋር ዉይይት በማካሄድ የህዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ፣ ምላሽ በመስጠት እና የቀጣይ የልማት እቅድ ላይ መወያየት በመቻሉ ህዝቡ ከፓርቲ ጋር ያለዉ መተማመን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል።

አቶ አደም አክለውም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዉ ምርጫዉ ከሂደት እስከ ዉጤቱ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ ቅቡልነት ያለዉ እንዲሆን እና ፓርቲያችን የጠራ ሀሳብ ለህዝብ አቅርቦ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ እንዲመረጥ ድርብ ሀላፊነት መወጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመድረኩ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት የተከናወኑ የፓርቲ ሥራዎች እቅድና አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ዉይይት የተካሄደበት ሲሆን የተመዘገቡ ስኬቶችን በማላቅ ድክመቶችን በማረም ተልዕኮውን በብቃት መፈጸም የሚችል ጠንካራ የፓርቲ ተቋም በመገንባት የኢትዮጵያና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያግዝ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party