“መጋቢት 24 በሀገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡”-የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር
“መጋቢት 24 በሀገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡”- ክቡር አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ
በድሬዳዋ አስተዳደር በለውጡ የተገኙ ድሎችና ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ።
በዚሁ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም ተሳታፊ ሆነዋል።
በከዚራ ለገሀር አደባባይ ለድጋፍ ለተገኘው ህዝብ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር እንዳሉት ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ታላላቅ ሀገራዊና አስተዳደራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ዕለቱ በተለያዩ የልማት መስኮች ድል ለማስመዝገብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው ያሉት ክቡር ከንቲባው፤ በዚህም ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረበት ሀገረ መንግስት በመገንባት ላይ መኮኑን ተናግረዋል።
የለውጡ ዓመታት ከፍተኛ የልማት መነሳሳት የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
በዚህም የለውጡ መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እመርታዎች መመዝገባቸውንም አመልክተዋል።
ሀገራችን የጀመረችውን ሁሉ አቀፍ የልማት ስራዎች ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከመንግስት ጎን በመሆን ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የለውጡ መሐንዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አመራር የመጡበት መጋቢት 24 በታሪክ አጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት የመጣ የድል ፍሬ ነው ብለዋል።
መጋቢት 24 በሀገራችን ኢትዮጵያ በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ እይታ አካታች፣ ህብረ ብሄራዊ፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተጠናከረበት አዲስ የፖለቲካ ስርዓት መስርተናል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለውም ዕለቱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማዕከል ያደረገ የመደመር መንግስት የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት የሀገረ መንግስት ግንባታ በይፋ የተጀመረበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባውም ጥሪ አስተላልፈዋል።
#prosperity