ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የሃሮ ደንዲ ሎጅ ምርቃትን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት
ዛሬ በኦሮሚያ ክልል የገበታ ለትውልድ መርሃግብር አካል የሆነውን የሀሮ ደንዲ ሎጅን በይፋ መርቀናል።
ይህ ስፍራ የተፈጥሮን ሥነ-ምህዳር የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ፣ ዘመናዊ ሥነ-ሕንጻ ከተፈጥሮ የልብ ትርታ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው። በዚህ ቦታ የቆመው ግንባታ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የተፈጥሮ ቅርሳችንን በማክበር፣ የደንዲ ክሬተር ሐይቅን ነባራዊ ውበት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተርፍ አድርገናል። ይህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴት ባከበረ እና ሰው ተኮር በሆነ መልኩ መሬቱን ለመንከባከብና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባ ስፍራ ነው።
የሀሮ ደንዲ ሎጅ፤ የገባነውን ቃል ፈጽመን የመገኘታችን ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው። ሎጅው እና የአካባቢው አስደናቂ ሥነ-ምህዳር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለሁነት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል።
ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ፣ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው!