የፓርቲያችን ማኒፌስቶ ዋነኛ ማዕከል የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ ተምሳሌታዊ ሀገር መገንባት ነዉ- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅ/ፅ/ቤት የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ብልጽግና በ7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችል ማኒፌስቶ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ማኒፌስቶው ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ ብልጽግና በማሸጋገር በአፍሪካና በዓለም ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን ፓርቲዉ ያለዉን ቁርጠኝነት ያመላከተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በብልጽግና ፓርቲ አመራር ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ስር ነቀል ለዉጦች በማስመዝገብ ላይ እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
ፓርቲው በመደመር ፍልስፍናዉ፣ በአሳታፊነቱ የታወቀና በህብረ ብሄራዊነቱ የደመቀ ፓርቲ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲያ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጣልበት፣ የህዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት በመሆኑ 7ተኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥተው እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ በበኩላቸው በሀገራችን ለዘመናት የነበሩ መንግስታት የዴሞክራሲ ስብራትን መጠገን ባለመቻላቸው ለዘርፈ-ብዙ ችግሮች ተዳርገን ቆይተናል ብለዋል።
ብልጽግና ባካሄደው ሀገራዊ ሪፎርም የዘመናት ስብራት የነበረው የዴሞክራሲ እጦት ከመጠገኑም በላይ አካታች ዴሞክራሲን መተግበር እንደተቻለ ገልፀዋል።
ብልጽግና በሀገራችን የነበሩ ፅንፍ አመለካከቶችን ወደ መሃል በማምጣት እዉነተኛ ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጎለብት ማድረጉን አስገንዝበዋል።
የፓርቲው ማኒፌስቶ ዋነኛ ማጠንጠኛ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሆነም አቶ ገ/መስቀል በንግግራቸው አስምረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ማኒፌስቶ ይፋ የተደረገ ሲሆን የመደመር፣ የብልፅግና፣ የልዕልና ትርጉም ያለው የብልፅግና ፓርቲ መለያ ምልክት 'የስንዴ ነዶ' በታላቅ ድምቀት ተዋውቋል።
በመርሃ ግብሩ የክልሉ የፓርቲና መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።