የዐርበኞች ድል መታሰቢያ እና የዘመናችን ዘርፈ-ብዙ የሉዓላዊነት ትርጉም
85ኛው የኢትዮጵያ ዐርበኞች የድል በዓል ሚያዝያ 27 ቀን በአራት ኪሎ የዐርበኞች የድል ሐውልት ሥር በድምቀት ሲከበር፥ ታሪካዊቷን ዕለት የምናስበው ያለፈውን ገድል በማድነቅ ብቻ ሳይሆን የዛሬውን እና የነገውን የሉዓላዊነት ትርጉም በወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አውድ ዳግም በመፈተሽ ሊሆን ይገባል።
ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን በደማቸውና በአጥንታቸው ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመድፈር የመጣውን የፋሺስት ጣሊያን ኃይል ድል ነስተው የሀገርን ዳር ድንበርና የፖለቲካ ነጻነት አስከብረውልናል። ይሁንና ብልፅግና ፓርቲ ሀገሪቱን እየመራ ባለበት በዚህ ዘመን የሉዓላዊነት ትርጉም ከድንበር ጠባቂነት ባሻገር ህልውናን በሁለንተናዊ መልኩ ወደ ማረጋገጥ ጽንሰ-ሀሳብ ተሸጋግሯል። የትናንቱ ዐርበኝነት የጠመንጃ እና ደረት የመስጠት ነበር፤ የዛሬው ዐርበኝነት ግን የማረሻ፣ የቴክኖሎጂ፣ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ተጋድሎ ነው።
እውነተኛ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው የራስን ጉርስ በራስ አቅም መሸፈን ሲቻል ነው። የትናንት ዐርበኞች ሀገርን ከቅኝ ግዛት እንዳዳኑ ሁሉ፤ የዘመኑ ዐርበኝነት ደግሞ ሀገርን ከረሃብ እና ከተረጂነት ማላቀቅ ነው። የምግብ እርዳታን የምትጠብቅ ሀገር፣ ፖለቲካዊ ሉዓላዊነቷ እና ብሔራዊ ክብሯ ዘወትር አደጋ ላይ ነው።
በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ቃል የጀመረው አገራዊ ንቅናቄ የዚህ ዘመን የሉዓላዊነት ግንባር ነው። በስንዴ ልማት፣ በበጋ መስኖ፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፈ-ብዙ የግብርና የልማት ስራዎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን (Food Sovereignty) በማረጋገጥ የውጭ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎችን እንድትቋቋም የሚያደርጓት ትክክለኛ የነጻነት ውጊያዎች ናቸው።
ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የፖለቲካ ነጻነት እና የሀገር ብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ዋነኛ መሳሪያ ነው። ብልጽግና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን በማጠናቀቅ እንዲሁም የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ዘርፎችን በማነቃቃት የኢትዮጵያን አቅም ለመገንባት እየሰራ ይገኛል። ይህ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጉዞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት እና ተሰሚነት ከፍ በማድረግ በማንም የውጭ ኃይል የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዳትሆን የሚያደርግ ወሳኝ ምሰሶ ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ የደህንነት እና የኢኮኖሚ ህልውና ቀጣይነት ከባህር በር ባለቤትነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና እጅግ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ግዙፍ ሀገር፣ አስተማማኝ እና የራስዋ የሆነ የባህር በር አማራጭ ማግኘት ለብሄራዊ ደህንነቷ እና ለቀጣይ ሉዓላዊነቷ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ብልፅግና ፓርቲ ይህንን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም በግልጽ በማንሳት እና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ በማድረግ ወደ መድረክ ያመጣው፥ የኢትዮጵያን ሙሉ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ነው። የባህር በር ማግኘት የሌሎችን ሉዓላዊነት የመድፈር ጉዳይ ሳይሆን፣ በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ህጋዊ የህልውና ጥያቄ ነው። ይህ የባህር በር ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ የትናንት አባቶች ያቆዩልንን ነጻ ሀገር፣ በጠንካራ እና በማይናወጥ የጂኦ-ፖለቲካዊ መሰረት ላይ የማጽናት ታሪካዊ አደራ ነው።
በአጠቃላይ 85ኛውን የዐርበኞች የድል በዓል ስናከብር የትናንቶቹን ጀግኖች ውለታ በማሰብ ብቻ ማቆም የለብንም። የዛሬው የዐርበኝነት መንፈስ የሚጠይቀው በላብ፣ በእውቀት እና በዲፕሎማሲ የሚደረግን አሸናፊነት ነው። ፓርቲው የነደፈው ዘርፈ-ብዙ የሉዓላዊነት ራዕይ—ከምግብ ራስን መቻል፤ እስከ ኢኮኖሚያዊ አቅም ግንባታ፤ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ የባህር በር ባለቤትነትን እስከማረጋገጥ የሚዘልቅ ነው። እኛም የዘመኑ ዐርበኞች በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ በምርታማነት፣ በአንድነት እና በጽናት በመቆም ይህንን ዘመናዊ የሉዓላዊነት ጉዞ ከዳር ልናደርሰው ይገባል።
ክብር ሀገራቸውን በደማቸው ላቆዩልን ዐርበኞቻችን! ክብር በላባቸው ሀገርን ለሚገነቡ የዘመናችን ጀግኖች!
እንኳን ለ85ኛው የዐርበኞች የድል በዓል አደረሳችሁ!
#prosperity