የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስጦታ አበረከቱ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን! በማለት ባስተላለፉት መልእክት ሁልጊዜም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው፣ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገነባናቸውን 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር በስጦታ አበርክተናል ብለዋል፡፡
በከተማችን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና ባህል እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት ነው። ይህንን በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ለደገፋችሁ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች በሙሉ በተለይም ከ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ላደረገው የኦሮሚያ ባንክ በተጠቃሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በትሳኤን ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል። ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ። መልካም በዓል! ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡