የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ መልእክት
የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስአበባ ማካሄድ ጀምረናል።
ከዛሬው መድረክ አስቀድሞ በትላንትናው እለት በአዲስአበባ ከተማ የተደረገው የመስክ ስራዎች ጉብኝት በከተማ አስተዳደሩ የተሰሩ የልማት ስራዎች የፓርቲያችን ዕሳቤዎች በላቀ መንገድ እየተሳኩ ስለመሆናቸው አመላካች ናቸው።
የብልፅግና ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ የተሰሩ ስራዎች ሁሉንም አቅሞች አሟጦ መጠቀም እንደሚቻል፤ መፍጠን መፍጠርና መዝለል ከተለያዩ ስራዎች አኳያ እንዴት እንደሚሳካ እንዲሁም እያንዳንዱን ስራ ከረጅም ጊዜ ራዕይ አኳያ እየመዘኑ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ ተመልክተናል።
በፓርቲያችን እሳቤ የህሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ በተሳካ አኳሃን እየፈጸምን መሆናችንን ያመላከተ ውጤት ተመልክተናል። ይህም መልካም ተሞክሮዎችን ወደሌሎች ለማሸጋገር የሚያግዝ ይሆናል።
2018 በጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት እና በልማት ሥራዎች ጉልህ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነው።
ከፓርቲ ግንባታ አኳያ ፓርቲያችን በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት እንዲሁም በማስፈጸም አቅሙ ተጠናክሮ የወጣበት ዓመት ሲሆን ድርብርብ ተልዕኮዎችን በታቀደው መሰረት ማሳካት የተቻለበት ነው።
መላው ሕዝባችንም በእያንዳንዱ ተልዕኮ ላይ በንቃት በማሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በመደረጉና በባለቤትነት ስሜት ከፓርቲያችን ጎን በመቆሙ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዟችን ጠንካራ መሠረት የጣለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ መንታ ግቦች በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል።
ልማትንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል።
በቀጣይም የፓርቲያችንን ግዙፍ አቅም አሟጦ በመጠቀምና የአመራር ስነ ምግባር ልህቀትን በማረጋገጥ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ መትጋት ይገባል።
በአዲሱ የበጀት አመትም የአመራርና አባላት ጥራት ማረጋገጥ፣ የብሄራዊነት ገዥ ትርክት ማስረጽና የፓርቲ ተቋማዊ ስታንዳርዳይዜሽን ስርዓት ግንባታ ማላቅ ላይ በተጠናከረ መንገድ ለመስራት የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች ርብርብ፣ የባለድርሻ አካላት ትብብር እና የመላው ሕዝብ ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ ነው።