የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ መልእክት
በዛሬው እለት በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሽንሌ ወረዳ ሲቲ ዞን ከወንድሜ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ ኡመር እና ከክልሉ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን የተሰሩ የልማት ስራዎች ጉብኝት እና የምረቃ መርሀ ግብር አካሂደናል።
እጅግ አስገራሚ በሆነ ፍጥነት በእድገት ጎዳና እየገሰገሰ በሚገኘው በሶማሌ ክልል ውስጥ በፓርቲያችን ፍሬያማ የለውጥ ትሩፋቶች ምክንያት በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስደናቂ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛል።
በሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ ውስጥም ህብረተሰቡን በስፋት ሊጠቅሙ የሚችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በክልሉ እና በፌደራል መንግስት ጥምረት እንዲሁም በግል ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
ለአብነትም ያህል በዋቢ ግሩፕ የግራናይት ፋብሪካ በነበረን ጉብኝት በክልሉ በማዕድን ኢንቨስትመንት እና በስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች በተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆናቸው ለመታዘብ ችለናል።
የግራናይት ፋብሪካው በዞኑ ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች የስራ እድልን ከመፍጠሩም በላይ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የግራናይት ውጤቶችን በስፋት አምርቶ በማሰራጨት ለውጪ ምንዛሬ ወጪ የሚዳርጉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ችሏል።
በመቀጠልም የጉብኝታችን መዳረሻ የነበረው በሽኒሌ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ሲሆን ሀገራችን ካሏት ወደ 60 ከሚጠጉ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካዎች መካከል ውስጥ አንዱ ነው።
በዚህም በጤናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆነውን የኦክስጅን ግብአት በማምረት ለሽኒሌ፣ ለአይሻ፣ ለቢኪ ሆስፒታሎች እንዲሁም አጠቃላይ በሲቲ ዞን ውስጥ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና ለድሬዳዋ አጎራባች አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሆነ የኦክስጅን ግብዓት ማከፋፈል ይችላል።
ከልማት ስራዎች ጉብኝት በተጨማሪ ከድሬዳዋ ሽኒሌ የተሰራውን የአስፋልት መንገድ መርቀናል። በቀጣይም መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራን ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተን የምንንቀሳቀስ ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ መንግስት ተገንብቶ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ የታመነበት፣ ወደ ጂቡቲ የሚሄደውን መንገድ ከመርማርሳ ከተማ የሚያገናኘውና በኮሪደር እሳቤ የሚሰራው የአስፋልት መንገድ መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠናል።
በአጠቃላይ በክልሉ የነበረን ቆይታ እጅግ ስኬታማ የነበረ ሲሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትጋት መስራታችንን እንደምንቀጥል እየገለፅኩ ለሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላደረጋችሁልን ደማቅ አቀባበል ያለኝን አክብሮት እና ምስጋና ለመግለፅ እወዳለሁ።