የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- አቶ አደም ፋራህ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ
ለሶስት ቀናት የሚቆየዉ 5ኛዉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ማስጀመሪያ መድረክ በአዲስ አለማቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።
በስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት: የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በተለያዩ መርሐ ግብሮች ከመከበሩ በተጨማሪ ተቋማቱ በሃገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ ያላቸውን የማይተካ ሚና በማጠናከር አጋርነታቸውን የሚያረጋግጡበት ነዉ።
አቶ አደም አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመንግስት ለተያዘዉ ሀገራዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራ ስትራቴጂያዊ አጋር በመሆን የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ በማረጋገጥ ገንቢ ሚና ከመጫወታቸዉ በተጨማሪ መንግስት በሚከተለዉ የብዘሃ-ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ እንደ አንድ ተዋናይ በመንቀሳቀስና የዘርፉን ክፍተቶች በመሙላት ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ተቋማቱ በትዉልድ መካከል እና በማህበረሰብ ዘንድ ሊኖር የሚገባውን ትስስር በማጠናከር ረገድ የሚጫወቱት ሚና የላቀ መሆኑን በማስታወስ ሃገራዊ ለዉጡን ተከትሎ በመንግሥት የተተገበሩ የህግ እና አሰራር ሪፎርሞችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱበትን ምህዳር በማስፋት አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እንዳስቻለም አስረድተዋል።
በሃገራችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ታሪክ አሁን የምንገኝበት ወቅት "ወርቃማው ዘመን" ተብሎ ሊገለፅ የሚችል እንደሆነና ተቋማቱ እርስ በርስም ሆነ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ትስስር በእጅጉ በማሻሻል አዎንታዊ ሚና መጫወት የሚችሉበትን እድል ማስፋት ያስቻሉ ስራዎች መተግበራቸዉንም በማስታወስ የተመቻቸውን እድል በመጠቀም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።
የለዉጡ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አፅንኦት ሰጥተዉ: ሃገራዊ መግባባትንና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን በማገዝ: ህዝባችንን ከተረጂነት ለማዉጣት የሚደረገውን ትግል በመደገፍና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎቻቸዉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች አንፃር በመቃኘት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ሃገራችን በኢፍትሃዊ አካሄድ ያጣችዉን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ በአለማቀፍ ደረጃ ተደራሽ እንዲሆን እና የአብዛኞቹን ሃገራት ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ በመወከል ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም ድርጅቶቹ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ በአደራ ጭምር አሳስበዋል።