የመደመር መንግሥት የዓለምአቀፍ ግንኙነት እመርታ፤ ለተምሳሌት ሀገር ግንባታ!
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ልዩ ሥፍራ ካላቸው ጥቂት ሀገራት አንዷ ነች፡፡ ሀገራችን ይህንን ልዩ ሥፍራ ለመያዝ የቻለችበት አያሌ ምክንያቶች ያሉ ቢሆኑም የጥንተ-ሰብ ምድረ-ቀደምትነትዋ፣ ጥንታዊ ሥልጣኔዋ፣ ስነ-መልክዓ ምድራዊ መገኛነትዋ እና የነጻነት ቀንዲ መሆንዋ ጎልተው የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እንኮ መገለጫዎች ሀገራችን በተለያዩ የዓለም ህዝቦች ምናብ እና ታሪክ ላይ ጉልህ ስፍራ ይዛ እንድትሳልና እንድትወሳ አስችለዋት ቆይቷል፡፡
ለምሳሌ ዓረቦች ኢትዮጵያን “የሐበሻ ምድር”፤ “የሰላምና የፍትህ ንጉስ የነገሰባት ሀገር” በማለት ያውቋታል፡፡ አውሮፓውያን ደግሞ “ፀሀይ ፊታቸው ያጠየማቸው ህዝቦች ምድር”፤“የንጉስ-ቄስ ዮሐንስ ሀገር” እንዲሁም “ሐበሻ” የሚለውን መጠርያ በመዋስ “አቢሲንያ” በማለት ሲጠሯት፣ በምናባቸው አግዝፈው ሲስሏት እና ለማየት ሲጓጓት ኖሯል፡፡ አፍሪካውያን በበኩላቸው “በራስዋ መሪ የምትደዳር የነጻነት ሀገር” እና “የአውሮፓ ቅኝ ግዛትን በአንድነት በመፋለም አሳፍራ የመለሰች የጀግኖች ሀገር” በማለት ሲያሞጉስዋት፣ ሲዘሙሩላት እና ምድሯን ሳይቀር በጫማችን መረገጥ እንደማይገባ በማሳየት ክብሯን ከፍ አድርገው ገልጸውላትዋል፡፡ በአጭሩ ጥንታዊት ኢትዮጵያ በመላ ዓለም ተምሳሌታዊት ሀገር ሆና በክብር እናገኛታለን፡፡
ኢትዮጵያን በዚህ መልኩ በታሪኳና በክብሯ ልክ የሚመለከታትና ሊያስቀጥላት የሚፈልገው የብልፅግና ፓርቲ እና የመደመር መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት እመርታ ለመፍጠር ከሰራባቸው መስኮች አንዱና ዋነኛው የዓለምአቀፍ ግንኙነት መስክ ነው፡፡ በለውጡ መባቻ “ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን” በሚል መሪ ቃል የታጀበው ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ራዕይ እንሆ በ7 ዓመታት ጉዞው አያሌ ስኬቶችን ተቀዳጅቶ በድምቀት መገለጥ ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የውጭ ግንኙነትን ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በማዳበል የሚመለከት ስጋት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ነበር፡፡ ይህ ፖሊሲ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደሚለው ሀገርኛ አባባል ከውስጥ የሚነሳ ጎምዛዛ የሰላም እጦትና የደህንነት ሥጋት የሚነሳ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነበረ፡፡ ይህ የጎረቤት ሀገራትንም ጭምር ከቻለ በቸልተኝነት ካልቻለ ደግሞ በስጋት የሚያይ እንደነበረ የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው፡፡
የለውጡ መንግሥት ይህንን የዓለምአቀፍ ግንኙነት ክልስ-ሀሳባዊ አተያይ ከስጋት-ወለድ/realist አተያይ ወደ ትብብራዊ/idealist እና ገንቢ/constructivist አተያይ በመቀየር አዲስ የፓርቲ ፕሮግራም እና የመንግሥት ፖሊሲ ቀይሶ ሲነቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ትብብራዊ/idealist የዓለምአቀፍ ግንኙነት አተያይ ሀገራት እና በተለያየ መንገድ የሚገለጹ ዓለምአቀፋዊ ተዋንያን በትብብር የመሥራት ፍላጎት አላቸው ከሚል በተስፋ-የተሞላ ዕሳቤ የሚነሳ ሲሆን ገንቢ/constructivist የዓለምአቀፍ ግንኙነት አተያይም በተመሳሳይ ዓለምአቀፍ ግንኙነት በዕሳቤና በተግባር የሚገነባ ነው ከሚል ዕሳቤ የሚነሳ ነው፡፡
በብልፅግና ፓርቲና በመደመር መንግሥት ተቋማዊ አቅም የተገለጠው ሀገራዊ ለውጥ ከዚህ የዕሳቤ ለውጥ በመነሳት አራት ስትራቴጂክ ጉዳዮችን በመለየት ሲተገበሩ ቆይተዋል፤ እነዚህም (1) ዜጋ-ተኮር መሆንና የዜጎችን ክብር መጠበቅ (2) ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ መሥጠት (3) ቀጣናዊ ትብብርን ማረጋገጥ (4) ዓለምአቀፋዊ ወዳጅነትን እና የዲያስፖራ ተሳትፎን ማስፋት የሚሉ ናቸው፡፡
በመጀመሪያው ስትራቴጂክ ጉዳይ የዜጎችን ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴና መሻት ለማሳካት እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚወድቁ ዜጎችን ከገቡበት ችግር እንዲወጡ ለማገዝ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለማጓጓዝ በተመደቡ አውሮፕላኖችም ጭምር ወደ ሀገራችን እንዲመለሱ በማድረግ ዜጎች በሀገራቸውና መንግሥታቸው ያላቸውን ተስፋ እንዲለመልም ማድረግ ተችሏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት በፖሊሲ እንዲመራና ይህንን የሚያስፈጽም ሚኒስትር መስሪያ ቤት ተቋቁሞ ዜጎች ተገቢውን ሥልጠና እየወሰዱ በህጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው ወደ ተለያዩ መዳረሻ ሀገራት ሄደው እንዲሰሩ በተደረገው ሀገራዊ ጥረት እስካሁን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲጓዙ ተደርጓል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የ5 ሚልየን ኮደርስ የሥልጠናና የሥራ ዕድል የሀገራችን ወጣቶች በቴክኖሎጂ ወደ ዳበሩ ሀገራትና ተቋማት ተጉዘው እየሰለጠኑ እና ገቢ የሚያገኙበትን ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያውን በስፋት እንታወቅበት ከነበረው የቤት ውስጥ ሥራዎች ባሻገር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙያዎች በሰፊው መሰማራት እንደምንችል እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 5 ሚልየን ገደማ የሚገመተው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ባለበት ሀገር በንቃት እንዲሰራ፣ ከሀገሩ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክርና ፍትሀዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት እራሱን የቻለ ኤጀንሲ ሆኖ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ኤጀንሲው ከረዥም ግዜና ጥረት በኋላ ተበታትነው የቆዩት የዲያስፖራ ማህበራትን ወደ አንድ ወጥ አደረጃጀት መሰብሰብን ጨምሮ የዲያስፖራው ተሳትፎ የሚያጠናክርባቸው እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጥባቸው ሥራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡
የአዲሱ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ፕሮግራምና ፖሊሲ ሁለተኛው ስትራቴጂክ ጉዳዩ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ ይህ አዲስ ፖሊሲ ጎረቤት ሀገራትን በስጋትና በጥርጣሬ ከመመልከት በመውጣት በታሪክ፣ በባህልና በኢኮኖሚ የሚተሳሰሩና በድንበር የሚዋሰኑት ጎረቤት ሀገራት ዋነኛ የልማት አጋር ለማድረግ ተንቀሳቅሶ እስካሁን አያሌ እመርታዎች ተገኝቶበታል፡፡ የኖቤል ሽልማት ማሳካት የተቻለበት የሰላምና ጸጥታ አጋርነት፣ የነጻ ንግድ ቀጣና ምስረታ፣ የወደብ አማራጭ ትብብር፣ የሀይል ትስስር እና ሌሎች የትብብር ማዕቀፎች በመተግበር አዲሱ የዓለምአቀፍ ዕሳቤያችን አያሌ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሎበታል፡፡
ቀጣናዊ ትስስር በሚያጠናክረው አዲሱ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ፕሮግራምና ፖሊሲ ሶስተኛው ስትራቴጂክ ጉዳይ በታላቁ የህዳሴ ግድባችን መጠናቀቅ፣ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) ገቢራዊነት፣ በተጠናከረው የኢጋድ ተሳትፎ፣ በሰላም ማስከበር የሚገለጹ አያሌ እመርታዎች መፍጠር ተችሏል፡፡ በአራተኛው የዓለምአቀፍ ግንኙነት ማስፋት ስትራቴጂክ ጉዳይ ረገድም በተመሳሳይ የብሪክስ አባል ሀገር ከመሆን ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች በማስተናገድ በፓርቲና በመንግሥት ደረጃ የሚገለጹ ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴዎችና ከፍ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ተቀዳጅተናል፡፡
በዚህ የብልፅግና መለያ እየሆነ የመጣው የሀሳብ ልዕልና የፈጠረው ተጨባጭ ተምሳሌታዊ ለውጥ በመታገዝ ኢትዮጵያ በG20 ጉባኤ ለመጀመሪያ ግዜ እንድትሳተፍ በክብር የተጠራችበት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በጉባኤው ወቅት ያደረጉት ንግግርና ውይይቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ከፍታና ተደማጭነት ወደ ላቀ ደረጃ የተሸጋገረ መሆኑ አሳይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጉጉት የሚጠበቀውን ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት COP32 ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ 6 ወር ብቻ የአያሌ ሀገራት መሪዎችና ልዑኮች ያስተናገደች ሲሆን ባለፈው ሳምንት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናኒንድራ ሞዲ ጉብኝት ኢትዮጵያን በታሪኳ ልክ የመግለጥ እና ተምሳሌታዊት ሀገር የማድረግ ራዕይ እየተሳካ መሆኑ አሳይቷል፡፡ ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት የምትፈልገውን የግንኙነት ደረጃ ወደ ስትራቴጂያዊ ትብብር እንዲያድግ መጠየቋ ደግሞ ኢትዮጵያ ስትመራበት የቆየችበትን ፖሊሲ ከፍተኛ ውጤታማነት ማሳያ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ሞዲ ጉብኝት ህንድ በቀጣይ ዓመት የብሪክስ ሊቀመንበርነት የምትረከብ ሀገር ከመሆንዋ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ከፍ ማድረግ መፈለግዋ አሳይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ተገኝተው የህንድና ኢትዮጵያ የስልጣኔ ትስስር፣ የንግድ ትብብር እና የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተመሳሳይነት መሰረት አድርገው ንግግር ማድረጋቸው የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ታይቷል፡፡ የፓርላማ ንግግሩ በኢትዮጵያ ያለውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን እምነት ያሳየ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህም የፊታችን ግንቦት 24 ግዜው ጠብቆ ነጻ፣ ፍትሀዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲካሄድ ዝግጅት እየተደረገለት ለሚገኘው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለው አንድምታ ትልቅ ነው፡፡
የታደሰው የኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ዕሳቤና ፖሊሲ በመተግበር በቀጣይ እዉን እንዲሆኑ እየተሰረባቸው ካሉ ጉዳዮች የባህር በር ማግኘት ጥረታችን አንዱና ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያን በታሪኳና ክብሯ ልክ እንድትገለጥ እና ወደ ተምሳሌት ሀገርነት እንድትደርስ የማድረግ የሀገራዊ ለውጡ ህዝባዊ አደራ ሳይጓደል በምልአትና በተግባር እየተገለጠ መሆኑን ህያው ምስክር ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ኢትዮጵያ ያላትን የሰላም ማስከበር የዳበረ ልምድና ለሥራው ያላትን ታማኝነት በሚመሰክር መንገድ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተፈጠረው የሰላም ችግር ለመፍታት ዓለምአቀፋዊ የሰላም ማስከበር ግብዣ እየቀረበላት ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን የሰላም ማስከበር ጥያቄዎች በፍትሀዊነትና በዓለምአቀፋዊ መርሆች በማጤን ስትሳተፍ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ሲሆን አሁንም ለታሪኳ በሚመጥን ደረጃ ምላሽ የምትሰጥ ይሆናል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት የዓለምአቀፍ ግንኙነት እመርታዎች የዕሳቤ ለውጥ በማምጣት አያሌ ስኬቶች እየፈጠረ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን የማድረግ እና በዓለም ያላትን ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ታሰፋለች፡፡
በዓለም ያላትን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በጥበብና በልበ-ሙሉነት በማቅረብ ያነገበችውን የሁለንተናዊ ብልፅግና ዓላማ ታሳካለች፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
ታህሳስ 13፤ 2018 ዓ/ም