Prosperity Party

እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ ተሰሚነት ለብሔራዊ ጥቅማችን መከበር አይተኬ ሚና አለው-ሳምንታዊ መልዕክት

የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ ተሰሚነት፣ ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት እና የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከኒው ዴልሂ እስከ ናይሮቢ፣ ከዋሽንግተን ዲሲ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተቀያየረ ባለው የዓለም ሥርዓት ውስጥ እየገነባችው ያለችውን ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት አንጸባርቃለች፡፡ ይህ ዓለምአቀፋዊ እመርታ ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ የዲፕሎማሲ ሁነት ሳይሆን በፓርቲያችን ብልፅግና እና በፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የመደመር መንግሥት የዓመታት ጥረት ውጤት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ (BRICS) ጉባኤ ላይ በንቃት በመሳተፍ እየተፈጠሩ ባሉ የብዙ-ዋልታ ዓለም አቀፍ መድረኮች እና በደቡብ-ደቡብ የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ ያላትን ሰፊ ሚና አሳይታለች። በናይሮቢ በተካሄደው የፈረንሳይ-አፍሪካ ጉባኤ ላይም ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት አስመስክራለች፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ አዲስ አበባ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽን እና የዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫን ጨምሮ በማስተናገድ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማነቷን አንጸባርቃለች። የእነዚህ መሪዎች ጉብኝት ለኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው ጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት እና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በሀገሪቱ አመራርና የሪፎርም ሂደት ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይ ነው።

ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት አዲስ እና ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በዋሽንግተን ዲሲ የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ውይይት (BSD) ማዕቀፍ መፈረሙ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ከመሆኑም በላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ወደ ላቀ ተቋማዊ እና ስትራቴጂካዊ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ስምምነቱ የኢኮኖሚ ብልጽግናን፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን፣ የመከላከያና ደህንነት ትብብርን እንዲሁም ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን ጨምሮ ወሳኝ ዘርፎችን ያጠቃልላል። ይህም ኢትዮጵያ ለቀጠናዊ መረጋጋት፣ ለኢኮኖሚ ሽግግር እና ለጂኦ-ፖለቲካዊ ትብብር ቁልፍ አጋር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ስትራቴጂካዊ እውቅና ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ከዋና ዋና የአሜሪካ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋማት (Think Tanks) ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፖሊሲ መድረኮች ላይ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ የሚያሳይ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ለዓለምአቀፍ ሁነቶች ምላሽ በመስጠት ብቻ የማትወሰን ይልቁንም በሰላም፣ በደህንነት፣ በኢኮኖሚ ውህደት እና በአፍሪካ ልማት ዙሪያ የሚደረጉ ቀጠናዊና ዓለምአቀፋዊ ውይይቶች ላይ የጎላ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ያሳያል፡፡

የእነዚህ ስኬቶች ማዕከል የመደመር የለውጥ ዕሳቤ ነው። መደመር የአካታችነት፣ የምክክር እና የጋራ እድገት ፍልስፍና ሆኖ በማገልገል የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ከተገዳቢነት (reactive) ወደ ንቁ ዓለምአቀፍ አጋርነት (proactive) መቀየር ተችሎበታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ልዩ አመራር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በእሳቸው አመራር ስር ኢትዮጵያ የሀገራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን በጽናት እየጠበቀች በሰላም፣ በጋራ መከባበር፣ በኢኮኖሚ ውህደት እና በዓለምአቀፍ ትብብር ላይ የተመሰረተ የውጭ ፖሊሲን እየተገበረችና ውጤት እያስመዘገበች ቀጥላለች፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተራ ተሳታፊ ሳትሆን የቀጣናዋ መጻኢ ዕድል የምትቀርጽ እና ለዓለምአቀፍ ውይይቶች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የምታበረክት እያደገች ያለች የዲፕሎማሲ ኃይል መሆኗ እያስመሰከረች ነው፡፡ እየተጠናከረ ባለው የዲፕሎማሲ አቅም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እየተከበረ ድምጿም በዓለምአቀፍ መድረክ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ የሚሳካ መሆኑ ከወዲሁ እየታየ ይገኛል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ
ግንቦት 10፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party