Prosperity Party

ኤሊት ፎርስ የምንገነባው ውጊያና ሽብር እንዳይፈጠር፤ ከተፈጠረም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ኤሊት ፎርስ የምትገነባው በቀጣናው ውጊያና ሽብር እንዳይፈጠር፤ ከተፈጠረም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት በሐዋሳ በድምቀት ተከብሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የልዩ ዘመቻዎች እዝ ቀይ ቦኔት ለባሾቹ ውጊያ የሚጨርሱ እና ውጊያ የሚያስቀሩ ናቸው ብለዋል፡፡

የእኛ ተልዕኮ ራዕይ ያለው ለትውልድ የሚሸጋገር ሁነኛ ተቋም መፍጠር ነው፤ ውጊያ የሚያስቀርና ውጊያ የሚጨርስ ኤሊት ፎርስ መገንባት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የልዩ ዘመቻዎች እዝ አባላት ተልዕኮ ደግሞ ኢትዮጵያን መገንባት፣ መጠበቅ፣ ማጽናት እና ማሸጋገር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ትሰራለች፣ በልጆቿ አጥንትና ደም ትጸናለች፣ አልተደፈረችም፣ አትደፈረም ፣ በክብርና በነጻነት ለልጆቻችን የምናስረክባት ብቸኛዋ የአፍሪካ ፈርጥ ሆና ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

የእኛ ዝግጅት በአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንዲሁም በቀጣናው ላሉ ሀገራት አለኝታና መከታ ለመሆን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለዚህም ሲባል በምድር፣ በተራራና በጅረት ይሰጥ የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አሁን ላይ ወደ ባሕር ቀይረነዋል ነው ያሉት፡፡

ከውሃ የመራቅ፣ ከውሃ የመሸሽ እና እንደ ባዕድ አምልኮ የማየት ክፉ ልማድ አሁን ባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የወንዝ ዳርቻ መሰል ልማት ሥራዎች መቀየሩን አመልክተዋል፡፡

ወንድም ሕዝቦችን ደግፈን ሽብርን ለመከላከል እና ልማት እና ብልጽግናን በቀጣናው ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም ያለው ኤሊት ፎርስ ገንብተናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም፣ በምሽግ ብቻ ሳይሆን በስተራቴጂክ ቦታዎች ውጊያን የሚያጧጡፍና የሚያሳጥር ተቋም ስለገነባች መላው አፍሪካውያን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኤሊት ፎርስ የምትገነባው በቀጣናችን ውጊያ እና ሽብር እንዳይፈጠር፤ ሲፈጠርም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party