Prosperity Party

ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው! እንኳን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቀን አደረሳቹ አደረሰን-ሳምንታዊ መልዕክት

 

ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2018 / መላው የሀገራችን ሕዝብ ከማለዳው 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመተመም ላይ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በበዓል ድባብ እና በነጻነት ተሞልተው መራጩን ሕዝብ በማስተናገድ ላይ ናቸው። ይህ ታላቅ ዕለት የፖለቲካ ሥልጣን ምንጭ የሕዝብ ሉዓላዊ ፈቃድ ብቻ መሆኑን በተግባር የምናረጋግጥበት፣ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አህጉሪቱ አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እየከፈትን ያለንበት ታሪካዊ ቅጽበት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ እየመረጠች ያለችው በራሷ ነባራዊ እውነታበጽኑ ብሔራዊ ክብሯ እና በሕዝቦቿ የላቀ ተሳትፎ ላይ ተመስርታ ነው፡፡

የሀገራችን የዴሞክራሲ ጉዞ የራሱ የሆነ ረጅምውስብስብ የታሪክ ምዕራፎች ያለፈ ነው። ቀደም ባሉ አስርት ዓመታት የታዩ የምርጫ ልምምዶች ሕዝቡ በነጻነት የመረጠበት ሳይሆን በቁጥጥርና በነጠላ ትርክት የታጠሩ እንደነበሩ አይዘነጋም። ሆኖም ኢትዮጵያ ካለፈችበት የታሪክ ተግዳሮት ተምራ ዛሬ ውጭ ጫናዎችን ያልተበገረና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ያስከበረ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

ይህ አዲስ ምዕራፍ በይዘቱም ሆነ በስፋቱ ከቀደሙት ሁሉ የተለየና ታሪካዊ እመርታ የታየበት ነው፤ 54 ሚሊዮን ጠቅላላ መራጮች ለመምረጥ የተዘጋጁበት መሆኑ ይህም ከ2013ቱ ምርጫ የ37 ሚሊዮን መራጮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የሀገሪቱ የፖለቲካ ንቅናቄ ምን ያህል እንደጎለበተ ያሳያል። ከዚህ አስደናቂ ቁጥር ውስጥ 46% የሚሆኑት መራጮች ሴቶች መሆናቸው ደግሞ የምርጫውን አካታችነትና ፍትሃዊነት በተግባር ያረጋገጠ ነው። በሌላ በኩል 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 10,438 ዕጩ ተወዳዳሪዎች በነጻነትና በሰላማዊ መንገድ ለውድድር ቀርበው ዛሬ ዕለት በሕዝብ እየተመረጡ ይገኛሉ። ይህ በመላ ሀገሪቱ የምናየው ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን የወደፊት ዕድላቸውንና የሀገራቸውን መጻኢ እጣ ፈንታ ለመወሰን በያዟቸው የምርጫ ካርዶች ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ እያካሄደችው ያለችው ምርጫ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ተምሳሌትነት አለው። የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ምሰሶ እና የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ መዲና እንደመሆኗ መጠን ይህንን ታላቅ የምርጫ ሂደት በራሷ አቅም ማከናወኗ አፍሪካውያን የራሳቸውን የቤት ሥራ በራሳቸው ለመከወን ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባት መቻላቸውን ማሳያ ነው። ይህንን ታሪካዊ ሂደት በዓይን እማኝነት ለመታዘብና አህጉራዊ አጋርነታቸውን ለመግለጽም የአፍሪካ ብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ከፍተኛ የታዛቢ ቡድኖች በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተሰማርተው ሂደቱን በንቃት እየታዘቡ ይገኛሉ። ይህ አህጉራዊ ተሳትፎ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የዴሞክራሲ ባህል እድገት የምታበረክተውን ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እና ፓን-አፍሪካዊ አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር ነው።

በየደቂቃው እያንዳንዱ ዜጋ ወደ ምርጫ ጣቢያ በማምራት በኮሮጆው ውስጥ የሚያኖረዉን ካርድ የሀገሪቱን አስተማማኝ ሰላም እና አጠቃላይ እድገት የሚወስን ነው። ዛሬ ህዝብ እየመረጠ ያለው በሰላማዊ የሃሳብ ውድድር የሚያምኑትን እና ህዝብን ያሻግራሉ የሚላቸዉን የፖለቲካ ቡዱኖችና መሪዎችን ቢሆኑም በድምሩ ግን አሸናፊ የምትሆነው ኢትዮጵያ ነች፡፡

የነገዋን የበለገች ኢትዮጵያ ለመገንባት ዛሬ በሰላም፣ በዲሲፕሊንና በብሔራዊ ኩራት ድምፃችንን እንስጥ፡፡ የምርጫው ውጤት በሚመለከተው አካል እስኪገለፅ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እና ውጤቱ በጸጋ መቀበል ደግሞ የሂደቱን ውጤታማነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም እስከ መጨረሻው የምርጫ ሂደት ድረስ የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት እና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንድናደርግ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የምርጫ ቀን ይሁንልን!

ብልፅግና ፓርቲ

ግንቦት 24 2018 /

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party