Prosperity Party

ኢትዮጵያ እንደ ወሎዬ ናት፤ በፍቅር ለመጣ ‘አርሂቡ’ በጠብ ለመጣ ‘አጋለይ' ትላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ልክ እንደ ወሎ ሕዝብ ሁሉ በፍቅር ሲመጡባት በእንግዳ ተቀባይነት የምታስተናግድ፣ በጠብ ሲመጡባት ደግሞ የማትበገር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን በመረቁበት ወቅት የወሎን ሕዝብ ማኅበራዊ እሴት ከሀገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት ጋር በማስተሳሰር መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ኢትዮጵያ እንደ ወሎዬ ሁሉ በፍቅር ለመጣ አካል እጇን ዘርግታ በፈገግታ እና በክብር "አርሂቡ" (እንኳን ደህና መጣህ) የማለት ትልቅ ባህል አላት። ነገር ግን፣ ሰላምን የማይሹ እና በጠብ የሚመጡ አካላትን ደግሞ "አጋለይ" ለማለት (ለመመከት) ለአፍታም አታመነታም ብለዋል። 

"ጠብ ከልማት እና ከብልጽግና ያስተጓጉላል፤ ጉዟችንንም ያራዝማል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "የምንፈልገው በፍቅር የመጣውን ‘አርሂቡ’ ብለን ማጉረስ ቢሆንም፣ ስንነካ ግን ኢትዮጵያዊ ደማችን ውስጥ ያለውን ‘አጋለይ' ማለትንም እናውቅበታለን" ሲሉ አስገንዝበዋል። 

የወሎ ሕዝብ በፈገግታው እና ሁሉንም አቃፊ በመሆኑ እንደሚታወቅ ገልጸው፣ ይህ መልካም እሴት ለተጀመሩ የልማት ሥራዎች ስኬት መዋል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል። 

ያማረች እና የበለጸገች ወሎን በጋራ መፍጠር፤ ወጣቶች ሳይሰደዱ በሀገራቸው የሚሠሩበትን ዕድል ማመቻቸት፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ በትጋት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። 

የወሎ ሕዝብ ላሳያቸው ልባዊ ፍቅር እና አክብሮት ልባዊ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። 

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party