ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦአካይ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አቀባበል አድርገዋል።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የገቡትን የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይን በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በመገኘት አቀባበል በማድረጋቸው ታላቅ ክብር እንደሚሰማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በቅኝ ግዛት ያልተገዙ፣ ለአኅጉሩ ነፃነትና አንድነት ድምፅ በመሆን ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ሁሌው ከሰፊ ገበታዋ ያላትን ታላቅ ዐቅምና ዘላቂ ወዳጅነት፣ አብረዋት ለሚጓዙ ሁሉ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው አረጋግጠዋል።
በዚህ መንፈስ የተከናወነው ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር፤የጋራ ህልሞችን በማይናወጥ መሠረት እና የመፈጸም ቁርጠኝነት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን ጽኑ እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል።