Prosperity Party

ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች እየተሰራች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)

ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ የማጽናት እና የመስራት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ ስፖርት ፓርክ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ግንባታ ስራ ሁለት መሰረታዊ ምሰሶዎችን መያዝ እንዳለበት ገልጸው፤ ትናንትን በወጉ እና በቅጡ የሚያስታውስ ነገን የሚሰራ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

በአድዋ ሙዚየም የአባቶቻችንን ጀግንነት እና  ነጻነታችንን እንደምናስታውሰው ሁሉ ነገን የምንሰራው በልጆቻችን ነው ብለዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ 35 ሺህ መዋዕለ ህጻናትን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቅሰው ዓላማውም የተሻለ ዝግጁነት ያለው ትውልድ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ግብ ነገን የሚሰራ ትውልድ ላይ ያተኮረ እንደሆነም ነው ያመለከቱት።

የሀገር ግንባታ እና የሰው ልማት የሚቆራኘው በአካዳሚክ እውቀት በሚገኝ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ መስተጋብር ጭምር ነው ብለዋል።

አዲስ ስፖርት ፓርክ እንደ አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ እና ጥሩነሽ ዲባባ ያሉበትን ሐውልቶች መያዙን ጠቅሰው፤ አትሌቶቹ ለትውልድ ምሳሌ የሆኑና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለአትሌቶቹ ሐውልቱ የቆመላቸው በህይወት እያሉ ማክበር ስለሚገባም ነው ብለዋል።

ፓርኩ በሁሉም መስክ ህጻናት እና ታዳጊዎች ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ ስፍራዎችን መያዙንና ይህም ትውልዱ ከአትሌቶቹ እንዲማር መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ህጻናቱ አትሌቶቹን መሆን እየተመኙ ተግተው ከሰሩ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚያስጠሩ አትሌቶችን ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ሳንዘራ ማጨድ አይቻልም ፣ መዋዕለ ንዋያ ሳናፈስ ውጤት መጠበቅ ከንቱ ምኞት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስመጥር ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደ አዲስ ስፖርት ፓርክ አይነት መሰረተ ልማቶች ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የስፖርት ፓርኩ በተለያዩ ስፖርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማቶች መያዙን ጠቅሰው፤ ይህም ለታዳጊዎች ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

ህጻናት ፓርኮች፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እና ንጹህ ስፍራዎችን እያዩ ካደጉ ሌላ ሀገር መሄድን መመኘት ትተው በሀገር መኩራትና መስራት እያደገ እንደሚሄድ ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ እንደምትገነባ ገልጸው፤ በሁሉም መስኮች ትናንት እና ነገን በማስተሳሰር ሀገርን መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝቧ ወጣት በመሆኑ ተግቶ መስራት እና ራስን በእውቀት ማበልጸግ ከታቸለ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን የመደገፍ ትቅል እድል እንዳለ አንስተዋል።

በክህሎት እና ብቃት ሰዎች ተሰርተው የሚያድጉበት መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የሚሰሩ ስራዎች የነገዋን ኢትዮጵያ እና ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የአዲስ ስፖርት ፓርክ የካዛንችስ መለወጥ እና ማበብን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው ፓርኩ ትውልድ የሚሰራበት ቦታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እየተሰራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ኢትዮጵያን የማጽናት እና የመስራት ተግባር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያን በመስራት ሂደት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party