Prosperity Party

ኢትዮጵያ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ሰጥታ ስትተገብራቸው የቆየቻቸው ሀገራዊ ንቅናቄዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል - አቶ አደም ፋራህ

በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ ጎንዮሽ በተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ፣ ኢትዮጵያ በሕፃናት ጤና አጠባበቅ፣ በሥርዓተ-ምግብ ማሻሻያ እና በምግብ ዋስትና ረገድ ያከናወናቸውን ስኬታማ ተግባራትና ተሞክሮዎች ለጋራ ምክክር አቅርባለች። 

በአፍሪካ የሕፃናት ጤና እና ሥርዓተ-ምግብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሥርዓተ-ምግብ ሻምፒዮን የሆኑት የሌሶቶ ግርማዊ ንጉሥ ሌቲ ሳልሳዊ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። 

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ሰጥታ ስትተገብራቸው የቆየቻቸው ሀገራዊ ንቅናቄዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፕሮግራሞቹ የተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦትን በማሻሻል እና የመቋቋም አቅምን በማጠናከር በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶችን እና ሕፃናትን ተጠቃሚ አድረገዋል ብለዋል። 

መንግሥት የተመጣጠነ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፣ ቀጣይነት ያለው ጥረት የወደፊት ትውልድ ደኅንነትን ለመጠበቅ እንደሚያስችል አፅንዖት ሰጥተዋል። 

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ፣ የጠየቁት አቶ አደም ፋራህ፣ በዚህም የአፍሪካ ብልጽግና መሠረት የሆነውን የሰው ኃይል በጋራ ማልማት እንደሚቻል ጠቁመዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሀገራት የተሻለ የሥርዓተ-ምግብ ፕሮግራሞችን እንዴት መተግበር እንዳለባቸው የኢትዮጵያን ተሞክሮ አጋርተዋል። 

በዚህም የሕፃናት ጤናን በማሻሻል፣ የሰቆጣ ቃልኪዳንን በመተግበር እና የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በማከናወን የተገኘውን አበረታች ውጤት አስረድተዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም ፋውንዴሽን መሥራች ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ በአህጉሪቱ የሕፃናትን አመጋገብ እና የሰው ሀብት ልማትን ለማሳደግ የፖለቲካ አመራር፣ ዘላቂ ፋይናንስ እና የአየር ንብረት ምላሽ ሰጪ ስልቶች አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተዋል። 

በመድረኩ በአፍሪካ ሥርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የሚረዳ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በአፍሪካ ሕብረት እና በኑትሪሽን ኢንተርናሽናል መፈረሙን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። 

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party