ኢትዮጵያን ወደ ኃይል ነጻነት የሚያሻግሩ 7ቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች!
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ፤ ሉዓላዊነቷንም የሚያስከብሩ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየሰራች ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ በመረቁበት ወቅት ኢትዮጵያ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የምትተገብራቸውን 7 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። 7ቱ የጉባ ብስራቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኢኮኖሚ አቅም ከማጠናከር ባለፍ ወደ ኃይል ነጻነት የሚያሻግሩ ናቸው። ይህም በሁኔታዎች የማይናወጥ፣ ለወቅታዊ የዓለም ገበያ ጫናዎች የማይበገር ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ህልሟን እውን ያደርጋል።
በሚቀጥሉት አምስት እና ስድስት ዓመታት የሚተገበሩ ሰባቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ለኢንዱስትሪው በምታመርተው ኃይል በራሷ የምትበቃ ሀገር ለመቀየር መሰረት ይሆናሉ።
በመጀመሪያ የኒውክሌር ማበልጸጊያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስገባታል። ይህ ፕሮጀክት ንፁህ እና ቀጣይ የሆነ የኃይል ምንጭ በመፍጠር የኢንዱስትሪ እድገትን ከመገንባት ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ አስፈላጊ ሚና ይጫወታል።
የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅና በሁለተኛ ደረጃ የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ የአገር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብትን ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ትልቅ በር ይከፍታል። ይህም የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ እንደሀገር ከውጭ ገበያ ምንጮች በሚገቡት ላይ ያለውን ጥገኛነት ይቀንሳል። በተጨማሪም የታሪክ እጥፋት በማምጣት ለውጭ ገበያ በመላክ ገቢ ማምጣት የሚችል እድል ይፈጥራል።
የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት እውን መሆን ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስመጣውን ነዳጅ በእጅጉ በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትን በመቆጠብ ኢኮኖሚውን ያጠናክራል። ፕሮጀክቱ ለኢንዱስትሪና ለትራንስፖርት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ከሰባቱ የጉባ ብስራቶች አንዱ የሆነውና በአፍሪካ ግዙፉ የአየር ማረፊያ ግንባታ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋና የአየር መጓጓዣ ማዕከል ያደርጋታል። ይህ ቱሪዝምን እና ንግድን በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ገቢ ይፈጥራል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታም በግብርና ዘርፍ የሚያመጣው ለውጥ ከፍተኛ ነው። የአገር ውስጥ ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ደህንነትን ከማረጋገጥ አልፎ የውጭ ጥገኛነትን ይቀንሳል።
ሰባተኛው 1.5 ሚሊዮን ቤቶች በመላው ሀገሪቱ መገንባት የከተማ ልማትን ያፋጥናል። በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ከመቅረፍ ባሻገር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን የስራ እድሎችን በመፍጠር የህዝብ ኑሮን ያሻሽላል።
በአጠቃላይ፣ እነዚህ ሰባት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ወደ ኃይል ነፃነት፣ ትልቅ ተስፋ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት እና የተሻለ የህዝብ ኑሮ ለመምራት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ይህ ጉዞ የጠንካራ እና በራሷ የምትቆም ኢትዮጵያን ለመገንባት በብልፅግና ፓርቲ የወደፊት ራዕይ ተቀርጾ የተመላከተ የሁለንተናዊ ብለጽግና ማረጋገጫ ግልፅ አቅጣጫ ነው።