ብልፅግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ነጥሮ እየወጣ በመሄድ ለውጡን ያፀና ፓርቲ ነው። የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ለ7ኛው ሀገራዊና አስተዳደራዊ ምርጫ ቅስቀሳ በሁለት የምርጫ ክልሎች የእግር ጉዞ አካሄደ።
“ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!” በሚል መሪ ሀሳብ 7ኛው ሀገራዊና አስተዳደራዊ ምርጫን በማስመልከት በዛሬው ዕለት የተካሄደው የዕግር ጉዞ መነሻውን ለገሀር አደባባይ መዳረሻውን ለገሀሬ አስታጥቄ ሜዳ አድርጓል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ዋልታ ረገጥና ከፋፋይ የፖለቲካ ስርዓትን ከሀገራችን ከመሰረቱ ለመቀየርና አዲስ የፖለቲካ ባህልን በመደመር እሳቤ ለመገንባት ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አሰባስቦ የተመሰረተ ፓርቲ ነው ሲሉ በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ለተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር የገለፁት የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ነጥሮ እየወጣ በመሄድ ለውጡን ያፀና ፓርቲ መሆኑንም ኃላፊው አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በውይይት መቋጨት መቻሉ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች አላቆ ማስመረቅ መቻሉ፣ ኢትዮጵያን ከስንዴ ተመፅዋችነት በማላቀቅ በአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራችነትና ወደ ላኪነት ማሸጋገር መቻሉ፣ በኮሪደር ልማት ስራ፣ በኢንደስትሪ፣ በቱሪዝም በርካታ ውጤታማ ስራዎችን በመስራት ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ታሪክ እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉም ተገልጿል፡፡
ብልፅግና ግልፅና ጉልህ የሆነ መንገድን በመከተል የባህር በር ጥያቄን በዓለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግና እንደ ብሪክስ ባሉ ዓለም አቀፍ ማዕቀፎች ውስጥ አባል በመሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገራዊ ብሄራዊ ጥቅሞችን ማስከበር የቻለ ፓርቲ መሆኑንም አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በአንክሮ ለተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ ነዋሪው በተግባር ተፈትኖ ውጤት ያስመዘገበውንና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር እያሸጋገረ የሚገኘውን ብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በእግር ጉዞ የተሳተፉ የፓርቲው ደጋፊዎች ብልፅግና ፓርቲ ሀገርን መምራት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ የምርጫ ምልክት ''የሰንዴ ነዶ'' እንደሆነና ምልክቱ የመደመር፣ አንድነትና ትብብር መገለጫዎችን የያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ክቡር ሀርቢ ቡህ፣ በተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ ተወካይ ዶ/ር ቢፍቱ መሀመድ፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ምክትልና የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ፣ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የድሬዳዋ ነዋሪዎች ታድመዋል።