ብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሀገሪቱ እድገት እየተጋ ነው- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት እና ሰባተኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሀገሪቱ እድገት እየተጋ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ባለፉት ስምንት አመታት አዲስ የለውጥ እሳቤን መሰረት በማድረግ ብልጽግና ፓርቲ ለአፍሪካ እና ለአለም ተምሳሌት የሆነ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።
ፓርቲው ጠቃሚ ሀሳቦችን በማመንጨት እንዲሁም ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ለኢትዮጵያ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በአብነት ጠቅሰዋል።
ፓርቲው የጀመረውን አሻጋሪ አመለካከት በማህበረሰቡ ውስጥ በማስረጽ ባለፉት ጥቂት አመታት በተከናወኑ ስራዎች የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው አመላክተዋል።
ከጋራ ትርክት ባሻገር የሚንጸባረቁ ነጠላ ትርክቶችን በማስወገድ በህዝቦች መካከል አንድነት መፍጠር ተገቢ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የጠምባሮ ህዝብ ከዚህ ቀደም የነበረውን በጋራ እና በትብብር ሰርቶ የማደግ እሴቱን ይበልጥ ማጎልበት እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ለሀገር ግንባታ ስራ መመካከር እና መወያየት አስፈላጊ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች እና ወጣቶች በጋራ እየተመካከሩ ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።
መመካከር እና መወያየት ለተጀመረው የእድገት ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ሀብታሙ በላይነህ እንደገለጹት የለውጡ መንግስት ሀገሪቱ ካጋጠማት ውስብስብ ችግር ማውጣት የሚያስችል ስርአት መዘርጋት ችሏል።
በልዩ ወረዳው ለበርካታ አመታት እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የተመለሰው በለውጡ መንግስት ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
በልዩ ወረዳው የሚገኙ ጸጋዎችን በማልማት እና በማስተዋወቅ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል።
በልዩ ወረዳው ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።