በፓርቲው የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው- አቶ አደም ፋራህ
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት 3ኛ ሩብ ዓመት ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በተካሄደው መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመሩ የልማት ኢኒሼቲቮች አፈጻጸም፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት አፈጻጸም በጥልቀት ተገምግሟል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በዚህ የግምገማ መድረክ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በበጀት ዓመቱ 3ኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የልማት፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነት ቅነሳ፣ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሥራዎች አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት በፓርቲው የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።
የልማት ኢኒሼቲቮችን በተመለከተ የተለያዩ አካላትን በማቀናጀት በህዝብ ንቅናቄ መምራት በመቻሉ የሚጨበጥ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
አቶ አደም አክለው እንደተናገሩት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች ናቸው።
በድጋፋዊ ሱፐርቪዥን የታዩ ጥንካሬዎችን ማስቀጠልና የተለዩ ክፍተቶችን በተቀናጀ መንገድ ማረም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ ከልማት ሥራዎች በተጨማሪ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅድመ ምርጫው ሂደት ፓርቲው እያከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አፈጻጸም በዝርዝር በመገምገም በቀሪ ቀናት ስለሚከናወኑ ተግባራትም አቅጣጫ ተሰጥቷል።