በወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አስደሳች ናቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ እና አስደሳች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ (ጊምቢ) እና በምስራቅ ወለጋ (ነቀምት) ዞኖች በመዘዋወር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወለጋ ሕዝብ ሰላም ወዳድ፣ ሥራ ወዳድ እና በፍቅር የተሞላ መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
"የወለጋ ሕዝብ ጠላቱ እንኳን ቢሆን ተጎድቶ እና ደክሞ ቢያይ ለመርዳት ልቡ የቀና፣ እጁ የተዘረጋ፣ ትምህርት እና ዕውቀት የሚወድ ሕዝብ ነው" ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙ ልክ ያልሆኑ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ አሁን ላይ ተጨባጭ የልማት ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ሕዝቡ እና አመራሩ ለሀገር ብልጽግና በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መከፋፈልን ማስወገድ፣ ሰላምን መጠበቅ እና ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"ወለጋ ዛሬ የደስታ ዝናብ የሚዘንብባት ምድር ናት" በማለት፣ ይህ መልካም ጅምር እንዳይስተጓጎል ሁሉም በጋራ ለሀገር ልማት እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።