በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ዛሬ መርቀን ከፍተናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)
በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው ይህ ዘመናዊ ተቋም ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ፤ ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ማዕከል ነው።
የምርምር ማዕከሉ 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስ (genomics) እና የባዮኢንፎርማቲክስ (bioinformatics) ቦታዎችን፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራትና ብቃት የሚያረጋግጥ የባዮኢኩዊቫለንስ (bioequivalence) ማዕከልን አካትቷል። በተጨማሪም ተቋሙ ለድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት አቅምን በመገንባት ረገድ እንደ ማገር ሆኖ ያገለግላል።
ምርምርን ወደ ፖሊሲ፣ ፈጠራን ደግሞ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር፤ ይህ ማዕከል በመድኃኒት ምርት ራሳችንን ለመቻል፣ ዘላቂ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ትልቅ እርምጃ ነው።