በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም የተሠራው ውጤታማ የመስኖ ሥራ ለሌሎች ክልሎችም አብነት ነዉ- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም በመስኖ የለማው የሣር መኖ እርሻ፣ የተፈጥሮን ልግስና በአግባቡ የመጠቀም ማሳያ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋር ክልል ዞን አንድ አይሳይታ ወረዳ የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም እየለማ የሚገኘውን የሣር እና መኖ እርሻ ጎብኝተዋል።
በወረዳው በ2 ሺህ 540 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ሣር የማምረት፣ የማቀነባበር እንዲሁም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተመልክተዋል።
ይህ የመስኖ ልማት ሥራ ለአካባቢው አርብቶ አደር የቴክኖሎጂ እና የተሻሻለ የዘር ሽግግር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በማሳው ላይ ለእንስሳት የወተት ምርታማነት ወሳኝ የሆኑ የሣር ዓይነቶች እየተመረቱ መሆኑም ተገልጿል።
የመስኖ ሣር ልማትና ማቀነባበሪያው ለ1 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሥራው ከእንስሳት ሀብት ልማት ባለፈ ለ"ሌማት ትሩፋት" ሀገራዊ መርሃ-ግብር ስኬት ታላቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም የተሠራው ውጤታማ የመስኖ ሥራ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ዝናብን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ ያሉትን ወንዞች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።