Prosperity Party

ሳምንታዊ መልዕክት

​​​​​​አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በጽኑ መሠረት ላይ የሚገነባ የትውልድ አሻራ ነው!
አለማችን በከባድ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በጎርፍና ድርቅ እየተፈተነች ባለችበትና ለችግሩ በተግባር የተደገፍ በቂ ትኩረትና መፍትሔ ባልተሰጠበት አስቸጋሪ ወቅት የሰዉ ዘር መገኛ የሆነችዉ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን እንደ መፍትሄ ይዛ ተከሰተች።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በ2011 ዓ.ም በፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ክቡር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረ ትልቅ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ሲሆን፤ አላማዉም የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሁለንተናዊ ብልፅግናን እዉን የማድረግ ሂደት ዉስጥ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕያችን አካል ነዉ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በ2011 ዓ.ም ለሰፊዉ ህዝብ ከተበሰረ እለት ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ በፖለቲካ አመለካከት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፆታ ሳንለያይ ከህፃናት እስከ አረጋዊያን፣ ከወጣቶች እስከ እናቶች/አባቶች ሁላችንም በአንድነትና በተባበረ ክንድ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸዉ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እንደ ትዉልድ አዲስ ታሪክ አስመዝግበናል።
ከዛም ባለፈ በአንድ ጀምበር ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አለማቀፍ ሪከርዶችን በመስበር ጭምር ልክ እንደ አድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የማሸነፍ እና የመቻል አቅም ለመላዉ አለም አሳይተናል።
የግብርና ሚኒስትር መረጃ እንደሚያመለክተው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከመጀመሩ በፊት የሀገራችን የደን ሽፋን 17.2 በመቶ አካባቢ የነበር ሲሆን፤ በተከታታይ በተደረጉ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ስራዎች የሀገራችን የደን ሽፋን አሁን ላይ ወደ 23.6 በመቶ አድጓል።
በሌላ በኩል በጥቂት ዓመታት ዉስጥ የምንተክላቸዉን ችግኞች ቁጥር ወደ 65 ቢሊዮን ከፍ በማድረግ የሀገራችን የደን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ስንቀን ወደ ፊት እየገሰገስን እንገኛለን።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የተተከሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ፓፓያ፣ ቡናና የመሳሰሉት ችግኞች የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ እና ለውጭ ኤክስፖርት ትልቅ አቅም እየሆኑ መተዋል።
እንደ ምሳሌም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ሪፖርት ሲያቀርቡ "ኢትዮጵያ 2018 ዓ.ም ብቻ ከቡና ምርት 3.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች። ባለፉት 17 ዓመታት ውስጥ ከተገኘው 3.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሊስተካከል ተቃርቧል። የዘንድሮው ገቢ ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 3ኛ ነው። ይህ የሪፎርም እና የአረንጓዴ አሻራ ውጤት ነው” ብለዉ መግለፃቸው ይታወሳል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር ስናየዉ ጥቅሙ የእትዬ ለሌ ነዉ፤ በመላዉ ሀገሪቱ ከ120,000 በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ዉስጥ ከ767,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድሎችን መፍጠር መቻሉን እና ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ወጣቶች መሆናቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዉድ ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ አሻራችንን ስናኖር የምንተክለዉ ዛፍ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ተክል ነገ አድጎ የገቢ ምንጭና የምግብ ዋስትናችን በመሆኑ ከኛም አልፎ ለልጆቻችን የሚተርፈዉን የእለት ምግባችንን ዛሬ እንትከል።
በእጃችን የምንተክለዉ ዛፍ አለምን በከፍተኛ ሁኔታ እየተነ ያለዉን የአየር ንብረት መዛባት ድርቅና ጎርፍን የምንዋጋበት አስተማማኝ መሳሪያና መጠለያ ስለሆነ ነገ ልጆቻችን የሚጠለሉበትን ጥላና የሚተነፍሱትን ንፁህ አየር ዛሬዉኑ እንትከልላቸዉ።
አሻራችንን ስናኖር ሁሉን አብቃይ ለም የተፈጥሮ አፈራችንን እየተንከባከብንና እየጠበቅን በመሆኑ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል መሬታችን ለምነቱን ጠብቆ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዟችን በአጭር ጊዜ እንዲሰምር ዛሬዉኑ ዛፍ በመትከል አሻራችንን ለትዉልድ እናኑር።
ዛሬ የምንተክለዉ ትንሽዬ ችግኝ የከርሰ ምድር ውሃን የምንቆጥብበትና ለሰዎች፣ ለእንሰሳት፣ ለዱር አራዊት፣ ለእፅዋት እና ለሁሉም ፍጡር ንፁህ የተፈጥሮ ምንጭ ዉሃን ከተራሮቻችን ስር ለማፍለቅ ዛሬ ችግኝ እንትከል፤ የተከልነዉን ተንከባክበን ለታለመለት አላማ እናዉል።
ባለፉት 7 አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተገኙትን ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በመላዉ ሀገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።
በዘንድሮዉ መርሃግብር ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 40 በመቶው ሀገር በቀል የደን ዛፎች ላይ ትኩረት ሲደረግ 60 በመቶው ደግሞ ለምግብ ዋስትናና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች የሚውሉ የፍራፍሬና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስትር የተገኘዉ መረጃ ያመልክታል።
ዉድ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በእጃችሁ የምትተክሉት ችግኝ በሁሉም ዘርፍ የበለፀገች፣ ልጆቿ ደስተኛ ሆነዉ በምቾት የሚኖሩባት፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ ታላቋን የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት ነዉና ይህን የክረምት ወቅት ሳናባክን በአግባቡ እንጠቀምበት። በእጃችን ሀገራችንን እንገንባ፤ ለመጪው ትውልድ ተስፋን በመትከል ታሪካዊ አሻራችንን እናኑር!
ብልፅግና ፓርቲ
ሀምሌ 6, 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party