ሳምንታዊ መልዕክት
የዴሞክራሲ ሽግግር የሚሳካው በህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እና በምርጫ ሂደት ብቻ ነው፤
የሀገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ አጭር ነው፡፡ በዚያ ላይ የፖለቲካ ባህላችን ሳይዳብርና ሳይዘምን ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ ሀገርና ህዝብ በተመኘነውና በሚገባን ልክ ወደ ፊት እንዳንራመድ ሲጎትተን፤ ወደ ፊት ለመሄድ ስንሞክር ደግሞ ጉዞው አፍርሶ የመገንባት የዜሮ ድምር መዳከር እየሆነ ብዙ ዋጋ ሲያስከፍለን ኖሯል፡፡ ይህ የዘመናት አዙሪት ለመቀየት የለውጡ መንግሥት አያሌ የአስተሳሰብ፣ የአሠራር እና የተቋማት ማሻሻያ አድርጓል፡፡
እነዚህ ማሻሻያዎች አያሌ ፈታኝ ችግሮች እንድንሻገር እና ሀገር ከመፍረስና ከብተና እንድንታደግ አስችለዉናል፡፡ ማሻሻያዎቹን እንደ ድልድይ በመጠቀም በአጭር ግዜ ዘርፈ ብዙ ለውጥና ዝላይ ተፈጥረው አይተናል፡፡ ህዝባችን እና የተለያዩ ታዛቢዎች ይህንን ችግሮችን የመቋቋም አስደናቂ ጉዞና የልማት እመርታ በተደጋጋሚ ሲገልጽና መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር የገለጠ በመሆኑ ሲያመሰግን ተመልክተናል፡፡ ይህ ጋህድ ሀቅ እና የወል እውነት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ እየታዩ ባሉ ንቁ ተሳትፎዎች ይበልጥ እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የይድረስ-ይድረስ ስብስቦችና ቡዱኖች ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመናድ ባቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ በቀን ሲቃዡ እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ የማይረዱ፣ ሀገር ሥርዓት መሆኑ የዘነጉ፣ ከግል ጥቅማቸው ውጭ የሀገርና ህዝብ ጥቅምና ህልዉና ግድ የማይሰጣቸው ህልመኞች አንዴ “የሽግግር መንግሥት” አንዴ “የግርግር መንግሥት” ይፈጠርልን በማለት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ሳይቀር ተልዕኮ በመቀበል ሀገር ለማፍረስና ህጋዊ መንግሥት እንዳይኖር ለማድረግ ሲፈጨረጨሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ የዘመናት የነውጥ መንገድ ያልተሳካላቸው የነጠፉ ፖለቲከኞች ይህንን ከንቱ ህልማቸው ለማሳካት ይሆናል ብለው የመረጡት ጊዜ የያዝነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መሆኑ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እና ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ያላቸውን ጥላቻ ያሳያል፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሀገር ለማፍረስና ሥርዓት አልበኝነት ለመፍጠር ያለሙ እኩይ ዓላማዎች በምርጫ ወቅት ሊሞከሩ እንደሚችሉ ሳይታለሙ የተፈቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም መንግሥት በቂ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን በመሥራት ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እያደረገ ይገኛል፡፡ መንግሥትና ህዝብ በአንድ ድምፅ “በምርጫ ብቻ” የሚል ግልፅና ጠንካራ አቋም በመያዝ እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድነት ለህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱና የዴሞክራሲ ሂደቱ ዘብ ቆሟል፡፡
ስለሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያን ለመምራት ፍላጎት ያለው አካል ሀገርና ህዝብ የመምራት ታላቅ ሀላፊነት በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለውድድር በመቅረብ የሥልጣን ባለቤት ከሆነው ህዝብ ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ መሆኑን መረዳትና መቀበል አለበት፡፡ ከዛ ውጭ በሚደረግ ማንኛዉም አፍራሽ ሙከራ በፍጹም የማይሳካ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተጠያቂነት የሚያስከትል ከባድ ወንጀል መሆኑ ግልፅ መሆን አለበት፡፡
“በምርጫ ብቻ”
ኢትዮጵያ ትመርጣለች፤
ህጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ታጸናለች፤
ብልፅግና ፓርቲ
መጋቢት 21፤ 2018 ዓ/ም