Prosperity Party

ሳምንታዊ መልዕክት

የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት መብት የሚረጋገጠው የመራጭነትን ካርድ በጊዜው በመውሰድ መምረጥ ሲቻል ነው፤

ዴሞክራሲ ሕዝቦች ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ማህበር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመርጡበት ሥርዓት ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 8 መሰረት ሕዝብ የሥልጣን የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሥልጣን በምርጫ እና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ የምንቀዳጀው ትልቁ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ለምርጫ ስኬት ደግሞ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በያዝነው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሟሟቀ በመሄድ ላይ ባለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28፤ 2018 ዓ/ም እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመራጭነት ለመመዝገብ ሦስት አማራጮችን ያቀረበ ሲሆን እነዚህም በ“ምርጫዬ” መተግበሪያ፣ በቦርዱ ድረ-ገጽ እና በምርጫ ጣቢያ በአካል በመገኘት የሚከናወኑ ናቸው፡፡ እነዚህ አማራጮችን በመጠቀም በመጀመሪያ ጥቂት ቀናት ብቻ ከ9 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ይበጃናል የሚሉትን ወኪል ለመምረጥ በነቂስ ወጥተው የመራጭነት ካርዳቸውን መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ገልጿል። በርካቶችም እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ፓርቲያችን ብልፅግናም ሰፊ አባላቱን፣ ደጋፊዎቹን እና መላው ህዝባችንን በተቀመጠው ቀነ ገደብ በመረጠው የምዝገባ አማራጭ በመጠቀም የመራጭነት ካርዱን እንዲወስድ እያበረታታ ይገኛል፡፡

ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት መብቱን መጠቀም የሚችለው በመራጭነት መመዝገብ እና የምርጫ ካርዱን በጥንቃቄ ይዞ በምርጫው ዕለት ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን መስጠት ሲችል ነው። ስለሆነም የመራጭነት መሠረታዊ መስፈርት የሚያሟላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም ሀገራችን ሕዝባዊና ሕጋዊ መንግሥት ለማፅናት በምታደርገው እንቅስቃሴ የዜግነት አስተዋፅኦዉን እንዲያበረክት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 

በምርጫ ብቻ! 
የመራጭነት ካርዳችንን በጊዜው በመውሰድ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ የነቃ ተሳትፎ እናድርግ!
ካርዳችንን በጥንቃቄ ይዘን በመቆየትም በምርጫው ዕለት የሚበጀንን ፓርቲ እንምረጥ! 

ብልፅግና ፓርቲ

መጋቢት 07፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party