Prosperity Party

ሳምንታዊ መልዕክት

እንመካከራለን፣ ችግሮቻችንን እንፈታለን፣ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንሻገራለን! 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት ሲከናወኑ የቆዩት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ባሳለፍነዉ ሳምንት፤ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ይህ የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በስፋቱ፣ በሂደቱ እና በሚያስገኛቸዉ ውጤቶች ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ አጀንዳዎች ተለይተው፣ ከአራት ሺህ በላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ስቻለ ረዥም እና ፈታኝ ጉዞ በኋላ፤ ኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መምከር ጀምራለች፡፡ በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ደጋግመን ሞክረነዉ፤ ደጋግመን የከሰርንበት የጠቅላይ-አግላይነት ፖለቲካ ማብቂያዉ አሁን ነዉ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዕለቱ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዘመናት ሲንከባለል የቆየው ስብራት በሃይለ-ቃል ተጀምሮ በሃይል እርምጃ የመደምደም ልማድ ነው፤ ይህን ስብራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው በምክክር፣ በንግግርና በይቅርታ ብቻ ነው። 

አጀንዳዉ ዛሬ ሃገራዊ ቅቡልነት አግኝቶ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩ የጋራ ስኬታችን ቢሆንም፤ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም አንስቶ ለኢትዮጵ ህዝብ የገባነዉ ቃልኪዳን አካል መሆኑን ግን ልብ ይሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመጀመሪያዉ በዓለ ሲመት ባደረጉት የፓርላማ ንግግር፣ በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያን "ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምዕራፍ እንሻገር" በማለት በይፋ ተናግረዉ ነበር። የአሁኑ ሀገራዊ ምክክር፤ ያኔ የተገባውን ቃል ወደ ተቋማዊ ትግበራ መሸጋገር የሚመሰክር ሲሆን፣ ሃገር-በቀል የሆነዉ እና ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር እሳቤ ዴሞክራሲያዊ ባህልን የመገንባት አቅም መጎልበቱንም በተጨባጭ የሚመሰክር ስኬት ነው። ልዩነትን በልክ የማስተናገድ፣ የመቻቻልና ልዩነትን በውይይት የመፍታት ልምምዳችን ዛሬ ፍሬ እያፈራ መሆኑ ደግሞ ሌላኛዉ ስኬታችን ነው። 

በሃገረዊ ምክክሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ ሃመር ወረዳ፣ ካራ ብሔረሰብ የተወከሉት ወ/ሮ ሙዶ አኮ ያስተላለፉት መልእክት ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የማንቂያ ደወል ነው። "ባለመነጋገራችን ብዙ" እንደከሰርን በማስታወስ፣ "እሳት ቤት የሚገነባ ቢሆን ኖሮ፤ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በተገነባች ነበር" ሲሉ ግጭትና ጥላቻ የጋራ ሃገር እንደማይገነቡ፣ ትብብርና ከልብ መደማመጥ ብቻ ለችግሮቻችን መፍትሄ እንደሆኑ መክረዋል። ይህ መልዕክት ላለፉት ዘመናት አጋር ተብለዉ፤ የዳር ተመልካች የነበሩ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ አቋም ነዉ፡፡ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የአሁኗ ኢትዮጵያ፤ የሁሉንም ዜጎች ድምጽ ማዳመጥ እንደጀመረችም አስረጂ ነው። 

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት እዚህ የደረሰዉ ያለ ተግዳሮት አይደለም። ኢትዮጵያ ስትገነባ ያልነበሩ፣ የውስጣችንን ልዩነት እና አለመግባባት የሚፈጥረዉን እድል ጠብቀው፤ በመካከላችን የልዩነትን ሽብልቅ ለመትከል፣ በዉስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የሚገቡ የዉጪ ሃይሎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። የ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ስልጣን የተቆጣጠረው በህዝብ ያልተመረጠ ቡድን የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ባለቤትነት ያሳጣበት፤ ሸፍጥ የተሞላበት ስታሪካዊ ህተት፤ ለዘመናት ለዘለቀው የሽብልቅ ጉዞ የቅርብ ጊዜ መገለጫ ነው።  

ያለፈዉ ታሪካችን የወለዳቸዉ ተግዳሮቶች እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን እስካሁን ቢፈትኑንም፤ ውስጣዊ ጉዳያችንን የሚወስኑበትም ሆነ ብሔራዊ ጥቅማችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉበት ዘመን አብቅቷል፤ ታሪካዊና ህጋዊ የሆነዉ የባህር በር የማግኘት ጥያቄያችንን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ከማረጋገጥ የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም። የከሰሩ የግጭት ነጋዴዎች እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪዎች አሁንም ጮፎሬ ተጫምተዉ ባረጀ የሽብልቅ ስልት ቢታትሩም፣ ኢትዮጵያና ልጆቿ በዉይይት እና ምክክር የጋራ ቤታቸውን እየገነቡ ነዉ፡፡  

ብልፅግና ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንዲሁም ዉሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ እያረጋገጠ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ ለራሱ ሳይሆን ለኢትዮጵያ፣ ለዛሬ ሳይሆን ለልጆቹ እንዲመክር ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ 

 

በምክክር ልዩነቶችን እናስወግዳለን!  

ተወያይተን አንድነታችንን እናፀናለን! 

ብልፅግና ፓርቲ 

ሐምሌ 13፤ 2018 ዓ/ም 

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party