ሳምንታዊ መልዕክት
ምርጫ የመግባባት ዴሞክራሲ ግንባታችን መሠረት ነው፤
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጎልተው ከወጡ የህዝብ ጥያቄዎች የመሬት፣ የማንነት እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የመሬት፣ የማንነት እና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ጥያቄዎች ከነአያሌ ችግሮቻቸውም ቢሆን ባለፈው ሥርዓት ለመመለስና ለማስተናገድ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ግን ከመጣንበት የፖለቲካ ባህል፣ ከዴሞክራሲ ብያኔ እና ትግበራ አንጻራዊ ልዩነት ጋር ተያይዞ በአግባቡ ሳይመለስ ቆይቷል፡፡
ከዛሬ ስምንት ዓመት ጀምሮ በመተግበር ላይ ያለው ሀገራዊ ለውጥ በአግባቡ መርምሮ እና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ለመሥጠት ከሰራባቸው ጉዳዮች የዴሞክራሲ ጥያቄ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጥያቄው በተሻለ ውጤታማነት እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ከበለጽጉ ሌሎች ሀገራት ጋር ለመስተካከል በሀገራችን ለዘመናት የቆየውን የባህል ስብራት መጠገን፣ ዴሞክራሲን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በአግባቡ መበየን እና ለሀገራችን ሁነኛ የሆነውን የዴሞክራሲ ዓይነት መምረጥ አስፈላጊ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር “የመግባባት ዴሞክራሲን” በጥንቃቄ በመምረጥ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፡፡
የመግባባት ዴሞክራሲ ባልዳበረ የዴሞክራሲ ባህል እና በግጭት ውስጥ ለቆዩ ሀገራት ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ የታየ ሲሆን ሦስት ዋና ዋና መገለጫዎች አሉት፤ እነዚህም አሳታፊነት፣ ፍትሀዊ ውክልና እና ራስን-በራስ የማስተዳደር ነጻነት ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት በመደመር ዕሳቤ የሚመራው የለውጥ መንግሥት ትክክለኛውን ጥያቄ በትክክለኛው መንገድ በመጠየቅ ኢትዮጵያ የምትሻገርበትን የዴሞክራሲ ዓይነት እየተገበረ ይገኛል፡፡
የመደመር መንግሥት ምርጫ አንድ ወሳኝ የመግባባት ዴሞክራሲ ግንባታ ምዕራፍ እንደሆነ ጽኑ እምነት አለው፡፡ ምርጫ በራሱ የመጨረሻ ግብ ባይሆንም እጅግ ወሳኝ ሂደት በመሆኑ የመግባባት ዴሞክራሲ ግንባታና ትግበራ መሠረት ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ መሠረት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ ምርጫን በማካሄድ ይህንኑ በተግባር መግለጥ ተችሏል፡፡
በውጤቱም በፖለቲካ ምህዳሩ መሥፋት ምክንያት የተፈጠሩት አያሌ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫ ማካሄድ እና ህዝባዊ ውክልናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህም በላይ አብላጫ ድምጽ በማግኘት መንግሥት የመሠረተው ብልፅግና ፓርቲ ለመግባባት ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በሚያሳይ መልኩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 7 የሚኒስትር ደረጃዎችን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ 275 የመንግሥት የሀላፊነት ቦታዎች ተመድበው ሀገር በመምራት ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ተግባር በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ታሪክ ውስጥ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ክስተቱም በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የዘመናት የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ አስተማማኝ የዕሳቤና የተግባር እንዲሁም የባህል ለውጥ መፍጠሩን በተግባር ያሳየበት ነው፡፡
በያዝነው ዓመት የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ የሚያጠናክርና የሀገራችንን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥረቶች ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድግ እንደሚሆን ጠንካራ እምነት አለን፡፡ ስለሆነም ምርጫ የመግባባት ዴሞክራሲ ግንባታችን መሠረት መሆኑን በመረዳት እና ይህንኑ በቀጣይነትና በዘላቂነት ለመገንባት ፓርቲያችን የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ከምን ጊዜም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ፤
ታህሳስ 20፤ 2018 ዓ/ም