Prosperity Party

ሳምንታዊ መልዕክት “ሚዲያ የሀገር መንፈስ ነው!”

 

ዓለምአቀፍ የሚዲያ ቀንን ምክንያት በማድረግ “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በተከታታይ ሳምንታት ሲካሄዱ የቆዩ ሚዲያ ላይ ያተኮሩ መድረኮች በዘርፉ የታዩት ስኬቶችንና በቀጣይ የሚጠበቁ ቁልፍ ተግባራትን በማመላከት በስኬት ተጠናቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ደማቅ የማጠቃለያ መድረክ ላይ ጥልቅ የሚዲያ ዕይታዎችና ዕሳቤዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ለዘርፉ ተዋንያንና ለመላው ህዝብም መልዕክቶች ተላልፈዉበታል፡፡

ከዕሳቤዎቹና መልዕክቶቹ መካከል ሚዲያ የሀገር መንፈስ መሆኑን የሚገልጽ ይገኝበታል፡፡ ይህ መንፈስ ሲታወክ ሀገር ትታወካለች፤ ሲረጋጋ ደግሞ ሀገር ታድጋለች፣ ትበልጽጋለች፡፡ በዚህ መሠረት ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከፈተው የዴሞክራሲ ምህዳር በዋናነት የተሰጠን ነፃነት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ጭምር ነው። የሚዲያ ጉዞው እንከን አልባ ባይሆንም የተመዘገቡት ስኬቶች እጅግ ግን ተስፋ ሰጪ ናቸው። በተለይ የሚዲያ ምህዳሩን በዲሞክራሲያዊ አውድ ለመዋጀት የተወሰዱ እርምጃዎች ለሀገር ግንባታ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል። ዛሬ ላይ ሚዲያዎቻችን ከጥላቻ ትርክት እና ከዋልታ ረገጥነት ወጥተው በእውነት ላይ የተመሰረተ ትረካ መገንባት የሚጠበቅባቸው ወቅት ላይ ናቸው።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባው ተመሳሳይ ሀሳቦችን በማስተጋባት ብቻ ሳይሆን ተቃራኒ ሀሳቦችንም በማስተናገድ ነው። ስለሆነም የሚዲያ አውታረ-መረቦቻችን የራስን ሀሳብ ብቻ ከመጫን ወጥተው ልዩነቶች በሰላም የሚስተናገዱበት መድረክ መሆን ይኖርባቸዋል። ባለፉት ዓመታት የታዩት ከፍተቶችም ትምህርት ሊሆኑን ይገባል። እውነተኛ የሚዲያ እመርታ የሚለካው በተለያዩ ሀሳቦች መካከል ድልድይ በመሆን እና ለብሔራዊ መግባባት በሚሰሩ ሥራዎች ነው። ሚዛናዊነትን የጠበቀ፣ ለህዝብ ቅርብ የሆነ እና ከተጽዕኖ ነፃ የሆነ አጠቃላይ የሚዲያ አውድ መፍጠር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን መሠረት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ዓለም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ትግል ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ሚዲያዎቻችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥልቅ ትንተና ማቅረብ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ መንግስት የገነባው ብሔራዊ የመረጃ ቋት "National Cloud" የቴክኖሎጂ መሠረት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነታችን እና የመረጃ ደህንነታችን መከታ ነው። ይህንን መሰረት በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሀሰት መረጃዎችን በመመከት እና የድህረ-እውነት ዘመን የሚያመጣውን የስነ-ልቦና ጦርነት በመጋፈጥ ረገድ ሚዲያው ግንባር ቀደም መሆን አለበት። ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ በጥናት የተደገፈ እና ለሀገር አዎንታዊ ገጽታ ለመገንባት የማይሳቀቅ ሚዲያ ለኢትዮጵያ የማይተካ አቅም ነው።

ሚዲያዎች ሙቀት ላይ ሳይሆን ብርሃን መፍጠር ላይ ማተኮር፤ ጫጫታ ላይ ሳይሆን የእውነት ምንጭ እና የሀገር መንፈስ መሆን አለባቸው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት “ሙቀት የሚፈጥሩ ሚዲያዎች ብርሃን መሆን አይችሉም”ና የሚዲያ አውታሮቻችን ከጊዜያዊ ገጽታ ግንባታና ቁንጽል ሀሳብ ሽያጭ ይልቅ ለሀገራዊ አጀንዳዎች እና የወል ትርክት ትኩረት በመሥጠት የብልፅግና መንገድ ጠራጊ እንዲሆኑ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

ብልፅግና ፓርቲ
ግንቦት 03፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party