Prosperity Party

ምርጫው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶችና ሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው!

በብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር የሴቶችና ወጣቶች የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ አባላት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው።   

ምርጫው ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሴቶችና የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት አመታት የሴቶች የአመራር ሰጪነት እና የፓለቲካ ተሳትፎ ያደገበት ሲሆን ሴቶች ይችላሉ የሚለውን ያረጋገጥንበትም  ነው፡፡ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አባላትን እንዲሁም ሕዝቡን በማንቃት የወጣቶችና የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

በሌላ መልኩ የወጣቶች የፖለቲካና የአመራርነት ድርሻ እንዲያድግ ከመደረጉም በላይ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት ተደርጓል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክላስተሩ የፖለቲካ ዘርፍ ሰብሳቢ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ ፓርቲው መሰረታዊ የዜጎችን ጥያቄ ከመመለስ አኳያ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የዴሞክራሲ ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችሉ ተቋማት መገንባታቸውንና እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ አንድነትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ይህም የዳር ተመልካችነት ቀርቶ ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሁሉም እኩል ሜዳ የሚረጋገጥበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርጫው ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ለማድረግ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party