ልጆች በሌላው ዓለም የሚገኘውን ሀገራቸው ውስጥ ካገኙ፤ በሀገር መኩራት እና በሀገር መጽናት እያደገ ይሄዳል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ የስፖርት ፓርክ የሀገራችንን ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ያሰናሰለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፓርኩ ትናንት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያኮሩ ጀግና አትሌቶችን ሐውልት የያዘ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ ጀግኖች አብዛኛዎቹ በሕይወት እያሉ ሲከበሩ ማየታችን በጣም መልካም ነው ብለዋል።
ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በሁሉም የስፖርት መስክ ታዳጊዎች ሊሠሩባቸው የሚችሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዘውተሪያዎች መገንባታቸውን አስረድተዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ሁሉም ዓይነት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ነገ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ጀግኖች እንዲወጡበት ታስቦ የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጸዋል፡፡
ዐዳጊዎች እነ ጥሩነሽ ዲባባን፣ ደራርቱ ቱሉን እና ቀነኒሳ በቀለን የመሳሰሉ ጀግኖችን ሐውልት እያዩ ልምምዳቸውን ሲሠሩ የነገ ተስፋቸው እጅግ ብሩህ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡
የዛሬ ልጆች ትናንት ያልነበረውን ማግኘታቸው ዕድለኛነታቸውን እንደሚያሳይ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ልጆች በሌላው ዓለም የሚገኘውን እዚሁ ሀገራቸው ውስጥ ካገኙ፤ በሀገር መኩራት፣ ሀገርን መውደድ እና በሀገር መጽናት እያደገ ይሄዳል" ብለዋል፡፡
ክህሎት እና ብቃት የአሁኑም ሆነ የመጪው ዘመን መሣሪያ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመንግሥት ዋነኛ ዓላማም የነገዋን ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ማሳመር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወጣት ኃይል ላይ መሥራት ከመጻኢ የኢትዮጵያ ተስፋም አልፎ አፍሪካን መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ፓርኩ የተገነባበት ቦታ እንዲህ ውብ እንደሆነው ሁሉ፣ ጠንክረን ከሠራን ኢትዮጵያም ከዚህ በላቀ ደረጃ ውብ እንደምትሆን ጠንካራ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡