ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በር የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነው
ጥር 04፤ 2018 ዓ/ም
ሀገራዊ ለውጡ በግንባር ቀደምነት ከመለሳቸው ህዝባዊ ጥያቄዎች አንዱና ዋነኛው የሀገራችን ፖለቲካ ምህዳር ማስፋትና የዴሞክራሲ ሥብራቱ መጠገን ነው፡፡ ይህ ለዘመናት ሲንከባለል የቆየው የህዝቦች የዴሞክራሲ መሻት ትርጉም ባለው መልኩ ለማርካት ከዚህ በፊት ያልተሄዱባቸው አዳዲስ መንገዶችና ያለተደፈሩ ቆራጥ እርምጃዎችና ንቅናቄዎች ተግባራዊ በማድረግ የታሪክ እጥፋት መፍጠር ተችሏል፡፡
ይህ የታሪክ እጥፋት በህዝብ የውጭ ግፊትና በአመራር የውስጥ ሳቢነት እንዲሁም በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ተባባሪነት የተፈጠረ ነው፡፡ እጥፋቱ በቅድሚያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የበላይ አመራሮች ሽግግርና የሥርዓት ማሻሻያ ማሳካት ተችሎበታል፡፡ በመቀጠል ደግሞ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ነጻ የማውጣት፣ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮቻቸው ወደ ሀገራቸው የመመለስ፣ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የቆዩ አካላት ከህዝባቸው ጋር በሰላም እንዲኖሩ የማድረግና የልማት ኃይል ሆነው እንዲቀጥሉ የማስቻል እንዲሁም መላ የሀገራችን ህዝብ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ተስፋው እንዲለመልም ተደርጓል፡፡
ይህ ተስፋ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻል አያሌ የዕሳቤ ለውጦች፣ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች፣ የተቋም ግንባታዎች እና አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባት፣ የሰፋ ፖለቲካ ምህዳር እና የተረጋጋ ሰላም እዉን ለማድረግ ተችሎበታል፡፡ ለውጡ ይህ ሁሉ ሲያሳካ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ይሁንና በተለያዩ የፈተና ወጀቦች ውስጥም ሆኖ የተነሳበትን ሀገራዊ ዓላማ ሲያሳካ ቆይቷል፡፡
ለአብነት “ተቃዋሚ” በመባል ይጠሩ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች “ተፎካካሪ” በሚል ዴሞክራሲያዊና ዘመናዊ ስያሜ በማስተናገድ በፉክክርና በትብብር መካከል ሚዛን እንዲኖር በማድረግ የተደመረና የተባባረ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እዉን ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ ሁኔታ ፖለቲካችን እንዲሰክን ያደረገ ብቻ ሳይሆን በትብብር መሥራት እንደሚቻል ያሳየ አዲስ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ትብብር በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በጉልህ የታየ ሲሆን መንግሥት ለህዝብና ለለውጥ ኃይሎች የገባውን ቃል በመጠበቅ 275 የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራር በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት እርከኖች እንዲመሩ በማስቻል ኢትዮጵያውን መተባበር የሚችሉ የአንድ ሀገር ልጆች መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ይህ የትብብር መንፈስ በዘንድሮው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመድገም ከማንኛውም ጊዜ በላይ አስተማማኝ መደላድል ተገንብቷል፡፡ በዚህ መሠረት ሀገራዊ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሀዊ፣ አሳታፊና ተአማኒ ከማድረግ በተጨማሪ የመላ ኢትዮጵያውያን የላቀ ትብብርና አንድነት ተጨማሪ መገለጫ እንዲሆን እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ የላቅ የዴሞክራሲ ዓላማ በምልዓት መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
ጥር 04፤ 2018 ዓ/ም