7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው- የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ዋና ጽ/ቤት ከፌደራል ተቋማት ብልጽግና ወጣቶች ክንፍ ጋር በመሆን የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶና መወዳደሪያ ምልክት ማስተዋወቂያ ፕሮግራም በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ ወጣቶች ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እንዲሁም ከምርጫ በኋላ ያላቸው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው መጻኢ ጉዞና ተስፋ ላይ ውሳኔያቸውን የሚሰጡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት አንዱ መገለጫ መሆኑን ገልጸው፣ በምርጫ ሥርዓት ውስጥ ወጣቶች እንደ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ዘርፈ ብዙ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
በፓርቲው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎችና ስኬቶች ውስጥ ወጣቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ከፍታ በሁሉም መስኮች ለማረጋገጥ ተግቶ እየሠራ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን አውስተው፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ እንዲሆን ወጣቶች በትጋት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫም በላቀ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሳካ አሁንም ወጣቶች በባለቤትነት መንፈስ በትጋት ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡