7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫን በማስመልከት በድሬዳዋ አስተዳደር በተሽከርካሪ የታጀበ የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ
በድሬዳዋ አስተዳደር 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫን በማስመልከት ከለገሀር አደባባይ እስከ መልካ ጀብዱ 20 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ከ1000 ሺህ በላይ ተሽከርካሪ የተሳተፈበት የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፍ በደመቀ መልኩ ተካሄደ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ብልፅግና ፓርቲ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ወደ ተጨባጭ ብርሃን የተሸጋገረ መሆኑን በድጋፍ ሰልፉ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል።
ከተማችን ሁሉም ሰው ተረጋግቶ የሚኖርባት የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ የመጣባትና በቀጣይም ይበልጥ የሚረጋገጥባት እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ ክቡር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል።
በቀጣይም ብልፅግና ካሸነፈ ከድህነት የምንወጣበትን መሰረት የምንጥል በመሆኑ የአስተዳደሩ ነዋሪ የነገ ዕጣ ፋንታውን በምርጫ ካርዱ ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ምክትል እንዲሁም የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ክቡር አቶ ሻኪር አህመድ ብልፅግና ፓርቲ ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተሰሩና በመሰራት ላይ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች ማሳያ መሆናቸውን በተመሳሳይ በድጋፍ ሰልፉ መርሀግብር ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።
በከተማዋ ለተመዘገበው ልማት የነዋሪው ድርሻ የላቀ መሆኑን የገለፁት ክቡር አቶ ሻኪር አህመድ አሁንም የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ባለው መልኩ እንዲጠናቀቅ ነዋሪው የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የድጋፍ ሰልፉን በማጀብ መርሀ ግብሩን ያደመቁት የከተማው ነዋሪዎች ብልፅግና ፓርቲ የኮሪደር ልማት፣ የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት፣ የኢንደስትሪዎችና ኢንቨስትመንት ማስፋፋትና ግንባታ፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም በርካታ ውጤታማ ስራዎችን በድሬዳዋ አስተዳደር ማከናወኑን በመግለፅ ለፓርቲው ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ ገልፀው የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፆ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።