"ብልፅግና ፓርቲ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ሁለንተናዊ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኝ ሰው ተኮር ፓርቲ ነው"- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በአርባምንጭ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ዞናዊ የምርጫ ቅስቀሳና ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ እና የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የምርጫ ወቅትን እየጠበቁ የህዝብ ተጠቃሚነት ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር በፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ከሚመጡ አሳሳቾች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠበቅ አሳስበዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ትላንት ስራ ላይ የነበረ ዛሬም ስራ ላይ ያለ ነገም ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር እየተጋ የሚገኝ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።
ነገ የተሻለች ሀገር የተሻለ ዞንና ከተማ እንዲኖረን የምንሻ ከሆነ ብልፅግና ፓርቲን ልንመርጥ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፓርቲው የሚገጥሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል እየቀየረ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
አርባ ምንጭ ከተማም ሆነ ጋሞ ዞን የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት መሆኑን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዞኑ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህብረተሰቡ ብልፅግናን ሊመርጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መላው የአከባቢው ህዝብ ቅድመ ምርጫ የምርጫ ወቅትና ድህረ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ግንቦት 24/2018 በሚካሄደው ምርጫ ህዝቡ ለብልፅግና ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ (ዶ/ር) ደምስ አድማሱ በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየተጋ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ሀገርን ተረክቦ መምራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በዞኑ በማህበራዊ በኢኮኖሚ እና ፓለቲካ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህም የፓርቲውን ፖሊሲ ትክክለኛነት ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ሀገራዊ አንድነት እንዲፀና እና ህብረ ብሄራዊነት እንዲጎለብት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዶክተር ደምስ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሠረተ ልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መላዉ የዞኑ ነዋሪ ለፓርቲው ድምፁን እንዲሰጥም አሳስበዋል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደ ሀገር 7ተኛው ሃገራዊ ምርጫ በአለም ህዝብ ዘንድ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተያዘው ግብ እንዲሳካ ከተማ አስተዳደሩ አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በከተማው የሚታዩና የሚጨበጡ የልማት ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ከንቲባው የተጀመሩ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማው ነዋሪዎች ፓርቲውን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ የብልፅግና ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች ፣ ከፍተኛ አመራሮች የብልፅግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
#prosperity