የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው!- ሳምንታዊ መልዕክት
በዚህ ወቅት በመላው ሀገራችንና በዓለም ፊት የተረጋገጠ አንድ ታላቅና የማይናወጥ እውነት ተፈጥሯል፤ እሱም በታሪካዊው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ቀዳሚ አሸናፊ ሀገራችን ኢትዮጵያ መሆንዋ ነው፡፡ ምርጫው እንደ ከዚህ ቀደም የተለመደው የፖለቲካ ውድድር ወይም ወቅታዊ ሁነት ሳይሆን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ያደመቀ፣ የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን ያጎለበተ እና መጻኢ የብልፅግና ጉዟችንን በጽኑ መሠረት ላይ ያቆመ ታላቅ የታሪክ እመርታ ሆኖ መውጣት ችሏል። ኢትዮጵያ በማንኛውም ውስጣዊ ተግዳሮት እና ውጫዊ ጫና ሳትበገር በራሷ ሁለንተናዊ አቅም ያከናወነችውን ይህ ታሪካዊ ፍጻሜ ተቋማዊ ጥንካሬን፣ ሀገር በቀል ዴሞክራሲን እና አህጉራዊ ሉአላዊነትን ያረጋገጠ የተምሳሌትነት ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህ ታላቅ ስኬትና ሀገራዊ ድል ብልፅግና ፓርቲና እና መንግሥት ያሳዩት ስልታዊ አመራር እና የላቀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ፓርቲያችን እንደ ህዝባዊ አደራ የተሸከመ እና እንደ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ በራሱ ደረጃ የምርጫ ዕቅድ በማውጣት፣ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን በመደገፍ እና አፈፃፀሙን በጥልቀት በመገምገም ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል፡፡ ምርጫው በስኬት ከተጠናቀቀ በኋላም የድህረ-ምርጫ ሥራዎች ላይ ግልጽ ዕቅድ አውጥቶ በብስለት እየመራው ይገኛል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና ታአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ምህዳሩን በሰፊው የከፈተ ሲሆን እውነተኛ ዴሞክራሲን ከተጨባጭ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ስኬቶች ጋር በማጣመር የሕዝብን ድምፅና ሉዓላዊ ፈቃድ ማክበር የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ይህም ሰላማዊና አካታች የሕዝብ ንቅናቄ እንዲፈጠር ከማስቻሉ ባሻገር አፍራሽና ጠላት ሀይሎች ምርጫውን ለማወክ ያደረጉትን መፍጨርጨር ለማምከን አግዟል፡፡
የዚህ ምርጫ ሌላው ድንቅና ተስፋ ሰጪ ገፅታ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት ከእነዚህም ውስጥ 46 በመቶው ሴቶች የሆኑበት ታላቅ ሂደት ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ማህበረሰብነት ምን ያክል ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማረጋገጫ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በነጻነት ቀርበው የተፎካከሩበት መድረክ መሆኑ ህዝቡ ሀገራዊ አማራጮቹን እና የወደፊት መሪዎቹን በሰፊው አመዛዝኖ እንዲመርጥ በር ከፍቷል። ይህ በመላ ሀገሪቱ የታየው የዜጎች መተማመን ኢትዮጵያውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ለመወሰን ያላቸውን ፅኑ እምነት ያረጋገጠ ነው።
የምርጫው አጠቃላይ ስኬት የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው፤ ስለሆነም ፓርቲያችን ብልፅግና ይህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ታሪካዊ ግቡን እንዲመታና ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የድርሻቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት የተወጡ ተቋማትን በታላቅ አክብሮት ያመሰግናል። ሂደቱን በገለልተኝነትና በከፍተኛ የባለሙያ ብቃት የመራውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለዴሞክራሲያዊ ባህል ዕድገትና ለሀሳብ ውድድር ሰላማዊና ኃላፊነት የተሞላበት ቁርጠኝነት ያሳዩትን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም ያለምንም የደህንነት ስጋት ሕዝቡ በነጻነት ድምፁን እንዲሰጥ ሌት ተቀን ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉትን የፌዴራልና የክልል ጸጥታ ኃይሎችን ያለንን ከፍተኛ ክብር መግለጽ እንወዳለን፡፡
መላ የፓርቲ አባላችን፣ አመራራችን፣ ደጋፊያችን እና ሀገር ወዳድ ዜጎቻችን እንደዚሁ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በታዛቢነት በመሳተፍ ለፓን-አፍሪካዊ አንድነትና ለሂደቱ እውነተኛነት ምስክርነታቸውን የሰጡትን እንደ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ያሉ ቀጣናዊና አህጉራዊ ተቋማትም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከልብ እናመሰግናለን። ስለምርጫው አድናቆታቸው የገለጹ የዓለምአቀፍ ማህበረሰቦች እና የሚዲያ ተቋማትም በተመሳሳይ ለምስክርነታቸውና ለአድናቆታቸው እናመሰግናለን፡፡
በቅርቡ በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው የፓርቲያችን የምርጫ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ላይ ክቡር ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እንደገለጹት ከሁሉ በላይ ታላቁ ምስጋናችን የሚገባው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለሀገሩ ህልውና ያለውን ፅኑ ወገንተኝነት በተግባር በማሳየት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሌሊት 10 ሰዓት ድረስ በረጅም ሰልፎች ላይ በሰላም፣ በትዕግስትና በከፍተኛ ዲሲፕሊን ቆሞ ድምፁን ለሰጠውና ለምርጫው ስኬት የሚችለውን ሁሉ ላደረገው ለተከበረውና ለአስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።
በአጠቃላይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ በማንኛውም ፈተና ውስጥ አልፋ ሉዓላዊነቷንና ተቋማዊ ጥንካሬዋን በራስዋ አቅም ማረጋገጥ የምትችል፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም መድረክ በሁለንተናዊ ግስጋሴ ውስጥ ያለች ታላቅ ሀገር መሆኗን ያስመሰከረችበት ነው።
ብልፅግና ፓርቲ በዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠበት እና ኢትዮጵያ ባሸነፈችበት ታሪካዊ ምርጫ የመሪነት ሚናዉን እንዲቀጥል ከሕዝብ አዲስ የዴሞክራሲ ኮንትራት ከተሰጠው የተጀመሩትን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በከፍተኛ ትጋት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ጉዞውን በበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ሊያረጋገጥ ይወዳል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
ሰኔ 01፤ 2018 ዓ/ም