Prosperity Party

የኢንዱስትራላይዜሽን እመርታችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር የማድረግ ውጥናችን የሚሳካ መሆኑ ማሳያ ነው- ሳምንታዊ መልዕክት

ፓርቲያችን ብልፅግና ቀምሮ በግልፅ ካስቀመጣቸው ፕሮግራሞች አንዱና ዋነኛው ኢኮኖሚን የተመለከተ ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ዓላማ ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ግቦቹም የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባት፤ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እና ምርታማነትን መሰረት ያደረገ ማህበራዊ ፍትህ ማረጋገጥ፤ ሀብትና ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ መገንባት እና ከተሜነት እና የከተማ ልማትን ማስፋፋት ናቸው፡፡ 
ኢኮኖሚው ከቆየበት የነጠላ-ዘርፍ ትኩረት ተላቆ ብዝሀ-ዘርፍ፣ ብዝሀ-ተዋንያን እና ብዝሀ-ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ የተቀመጠለት የሪፎርም አቅጣጫ በመከተል እስካሁን አያሌ አስደናቂ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ከእነዚህ የብዝሀ-ዘርፍ አውታሮች አንዱ የሆነው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሲሆን በዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን የ3-2-1 ኢኒሼቲቭ ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ በነዚህ ንቅናቄዎች አማካኝነት ተኪ ምርት ከማምረት፣ በሚልዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት፤ ሀብት ፈጠራና የቤተሰብ ብልፅግና ከማረጋገጥ አልፎ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግርና ሉአላዊነት እየተገነባበት ይገኛል፡፡
በቅርቡ የገላን ጉራ የኢንዱስትሪ ፓርቲ ሥራ መጀመር እና በሞጆ ከተማ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ወደ ማምረት የገባው ግዙፍ የሴራሚክስ ማምረቻ ፋብሪካ የዚህ ውጤታማ የኢንዱስትራላዜሽን ጉዟችን ማሳያ ናቸው፡፡ ክቡር የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብይ አሕመድ በሞጆ የሴራሚክ ፋብሪካ ምረቃ መርሀግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ4.85 ቢልዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለበት መሆኑ ጠቅሰዋል፤ የሴራሚክ ፋብሪካው መከፈቱ የውጭ ምርት ጥገኝነት የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላትም ጭምር መሆኑ ገልጸዋል፡፡
የማኑፋችሪንግ ኢንዱስትሪ ስኬቶች በአጠቃላይ ሲታይ በዘርፉ በ2010 በጀት ዓመት የነበሩትን 18,747 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአሁን ወቅት 27,764 ማድረስ ተችሏል፡፡ የማምረት አቅም አጠቃቀም 2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 46 በመቶ በ2018 ግማሽ ዓመት ወደ 66.3 በመቶ ደርሷል፡፡ የኤክስፖርት አፈፃፀም 2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 308.12 ሚሊየን ዶላር  የውጭ ምንዛሬ የተገኘ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት 380 ሚሊየን ዶላር ደርሷል፡፡ ባጠቃላይ የአምራች ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዕድገት 2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 5.5 በመቶ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 10.7 በመቶ በእጥፍ አድጓል፡፡ 
በቀጣይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አማካኝ ዕድገት 22.9 በመቶ፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ድርሻ 17.2 በመቶ እና የማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ገቢ 8.9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዘርፉ የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ 60% እና የሚፈጠው የሥራ ዕድል 5 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል፡፡
ይህ በአጭር ጊዜ የተፈጠረ እመርታ ዘርፉ ለብዙ አስርት ዓመታት ሲያሳይ የቆየውን አዝጋሚ ለውጥ በመሰረታዊነት የቆየረ ነው፡፡ ይህም በትክክለኛ ዕሳቤ እና ፕሮግራም መመራት እንዲሁም ለሀገር ዕድገት በቅንነትና በቁርጠኝነት መሥራት እመርታዊ ለውጥን እዉን ለማድረግ እንደሚያስችል ያሳየ ነው፡፡ ይህ ተሞክሮ ብልፅግና ፓርቲ የቀጣይ አምስት ዓመታት የዴሞክራሲ ኮንትራቱን በማደስ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን የሰነቅነዉን ዓላማ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ይጠቀምበታል፡፡
ስለሆነም በዚህ አስደናቂ የብልፅግና የለውጥ ጉዞ ላይ በቀጣይነት አሻራችንን በማኖር የታሪክ ሰሪነት ክብራችንን አጠናክረን እንዲንቀጥል በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡ 
ብልፅግና ፓርቲ
ግንቦት 17፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party