የኢትዮጵያ አዲሱ የዲፕሎማሲ አድማስ እና የመደመር ድሎች
በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በአንድ ዋልታ ረገጥ ሥርዓት ማክተሚያ እና በባለብዙ ዋልታ ሥርዓት መባቻ ላይ ትገኛለች። ይህ ሽግግር ለታዳጊ አገራት፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ቀጠናዊ ኃይሎች፣ አዳዲስ የዲፕሎማሲ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል። በዚህ ፈጣንና ተለዋዋጭ የዓለም ዑደት ውስጥ የብልፅግና ፓርቲ የውጭ ግንኙነት መርህ መደመርን መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያን ከተረጂነትና ከከበባ ፖለቲካ አውጥቶ ወደ ቀጠናዊ ተምሳሌትነትና መሪነት እያሸጋገራት ይገኛል።
ባለፉት ዘመናት የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ በጥርጣሬና በውስጥ ስጋት ላይ የተመሠረተ ተከላካይ ነበር። የመደመር ፍልስፍና ግን ይህን ቀይሮታል። መደመር በዓለም አቀፍ ግንኙነት የታወቁትን እውናዊነት እና ሊበራሊዝምን በማስታረቅ አዲስ መንገድ ቀይሷል።ይህ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በኃያላን አገራት ፉክክር ውስጥ ሳትወግን፣ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል አድርጋ እንድትጓዝ አስችሏታል።
ሌላው የብልፅግና ትልቁ ድል የዲፕሎማሲውን ማጠንጠኛ ከፖለቲካዊ ልመና ወደ ኢኮኖሚያዊ አጋርነት መለወጡ ነው። ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል (ኤሌክትሪክ) ያላትን እምቅ ሀብት ለጎረቤት አገራት (ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን) በማቅረብ የቀጠናው የኃይል ቋት እየሆነች ነው። ይህ የኃይል ትስስር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ ጎረቤቶቻችን በኢትዮጵያ ሰላም ላይ ያላቸው ድርሻ ከፍ እንዲል በማድረግ ስትራቴጂካዊ ዋስትናን ፈጥሯል። የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችም አገሪቱ ለወደፊቱ ያላትን የኃይል ራዕይ የሚያሳዩ ናቸው።
በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን የጽናት አርማ ብቻ ሳይሆን፣ የዲፕሎማሲያዊ ድል ማሳያም ነው። ኢትዮጵያ “ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም” የሚለውን ዓለም አቀፍ መርህ በተግባር አረጋግጣለች። የግድቡ ስኬት አገሪቱ በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ያላትን የመሪነት ሚናም ያጎላ ነው፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ የመልክዓ-ምድር እስረኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ብልፅግና በግልጽ አስቀምጧል። ይህ ጥያቄ የጦርነት አጀንዳ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ፍትህና የህልውና ጥያቄ ነው። አገሪቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት፣ ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ ስህተት ማረሚያ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ በብልፅግና መሪነት የምትከተለው የውጭ ግንኙነት መንገድ፣ አገራዊ ክብርን ማስጠበቅ፣ ወዳጅ ማብዛትና ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የብሪክስ አባል መሆን፣ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ተሰሚነቷ ማደጉ ኢትዮጵያ የችግር ምንጭ ሳይሆን የመፍትሔ መዳረሻ መሆኗን ለዓለም አሳይቷል።
የመደመር ዲፕሎማሲያዊ ጉዟችን ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ማድረሱ አይቀሬ ነው፤ ምክንያቱም መሠረቱ እውነት፣ ፍትህና የጋራ ብልፅግና ነውና!
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!