የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚየም የጀግንነታችን ማኅደር፣ የልዕልናችን ምስክር ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው። ዛሬ በጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዝየም ስንጎበኝ፣ ይሄንን የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚመሰክሩ ህያው አሻራዎችን ተመልክተናል።
ከ1950ዎቹ ጀምሮ እንዲቋቋም ሲታለም የቆየው ይህ የጦር መዝየም፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ብቅ እልም ሲል ቆይቶ ዛሬ በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት ተቋማዊ ቁመና ተላብሶ እውን ሆኗል። ይህ ስኬት ለሚገነባው ግዙፍ ብሔራዊ የሠራዊት ሙዝየምም እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚወሰድ ነው።
ከዓድዋ ዘመን በፊት የነበሩ ብርቅዬ መሣሪያዎችና የነገሥታቱ ትጥቆችን ጨምሮ በሙዚየሙ ያሉት የጦር ታሪክና ቅርሶች የጀግኖቻችንን ታሪክ ይዘክራሉ።
ከ1900 ጀምሮ ያለውን ዘመናዊ የተቋም ግንባታ፣ የጦር መሣሪያዎች ዝግመተ ለውጥና መከላከያችን የደረሰበትን አስደናቂ የምህንድስና ጉዞ የሚያስቃኘው ይህ ማዕከል፤ ለሠራዊቱና ለትውልድ ታሪክን፣ ዕውቀትንና መነሳሳትን የሚያስታጥቅ ነው።
በሙዝየሙ፣ ከትናንቱ እንማርበታለን፤ ዛሬን እንገመግምበታለን፤ ለነገ ደግሞ እናቅድበታለን። አፍሪካውያንና መላው በፀረ ቅኝ አገዛዝ የታገለ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ይሄንን ሙዝየም በመመልከት የራሱን ታሪክ እንዲያደንቅ እጋብዛለሁ።
የኢትዮጵያ ሠራዊት የታሪካችን ኩራት፣ ከሀገር አልፎም በዓለም ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳ የሰላም ዘብ ነው።የታሪካችን ድምቀት የሆነው የሠራዊታችን ገድል ለትውልድ እንዲሸጋገር በዘመናዊ መንገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ በመሆናቸው፣ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።