የኢትዮጵያ ማንሰራራት በዓለም ባንክ አንደበት
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ዕውቅናን እያገኘ ይገኛል። በተለይም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን መልሶ የማደራጀትና የማዘመን ሂደት፣ አገሪቱ ካጋጠሟት ውስብስብ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ወጥታ ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኑን የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
ከሰሞኑ የዓለም ባንክ “ከበጀት ጫና ወደ ኢኮኖሚ ሞተርነት” በሚል ያወጣው ዘገባ፣ ኢትዮጵያ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ረገድ ያከናወነችው ተግባር ለሌሎች ታዳጊ አገራትም እንደ ሞዴል ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን አረጋግጧል።
ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ግልጽነት በጎደለው አሠራር፣ በዕዳ ክምችት እና በከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ የሚታወቁ ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ2021 የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አብዛኞቹ ተቋማት የኦዲት ሪፖርት እንኳ የሌላቸውና ለመንግሥት ካዝና ትርፍ ከማስገባት ይልቅ ጫና የሚፈጥሩ ነበሩ። ሆኖም ግን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት የወሰደው ደፋር የሪፎርም እርምጃ ይህን ታሪክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀይሮታል።
የዓለም ባንክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሚያዝያ 2026 ባወጣው ግምገማ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 117 ቢሊዮን ብር (720 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) በግብር እና በትርፍ ድርሻ መልክ ለብሔራዊ በጀቱ ገቢ አድርገዋል። ይህ ቁጥር ተቋማቱ አገሪቱን ከመመገብ አልፈው፣ ለታላላቅ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆን የፋይናንስ አቅም እየፈጠሩ መሆኑን ያሳያል።
ይህ ስኬት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ በ“መደመር” ፍልስፍና የታገዘ መዋቅራዊ ለውጥ ውጤት ነው። የኢትዮጵያን ግዙፍ ሀብቶች በአንድ ላይ በማሰባሰብ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) የሪፎርሙ ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ ተገኝቷል። ተቋሙ የመንግሥት ሀብቶች እንደ ግል ድርጅቶች በውጤታማነትና በንግድ መርህ እንዲመሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በተጨማሪም የዓለም ባንክ ምስክርነት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመረጃ ቋት በመፍጠር እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን (IFRS) ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያሳየችው ቁርጠኝነት፣ በዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ዘንድ በአገሪቱ ላይ ያለውን አመኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል።
የሪፎርሙ ዋነኛው ዓላማ የፋይናንስ መረጋጋት ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገራዊ ጫናነት ተላቀው ወደ ትርፋማነት ሲሸጋገሩ፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የመክፈት አቅማቸው እያደገ መጥቷል። የዓለም ባንክ አመራሮች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ “ጠንካራ የመንግሥት አመራርን ከታለመ ድጋፍ ጋር በማጣመር” የግል ዘርፉ እንዲሳተፍና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች።
በተለይም እንደ ቴሌኮም እና ኢነርጂ ያሉ ዘርፎች ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸው፣ አገሪቱ ከዘመኑ ጋር የደረሰ የዲጂታል እና የኢንዱስትሪ ልማት ባለቤት እንድትሆን መንገዱን ጠርጓል። ይህ ሂደት ኢትዮጵያ የነበራትን የመንግሥት የበላይነት ወደ መንግሥት የሚያመቻቸው የገበያ መርህ (State-enabled market) በመቀየር ረገድ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በኢትዮጵያ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ያላቸው እምነት እያደገ መምጣቱ፣ አገሪቱ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ትክክለኛ መሠረት ላይ መሆኑን ያረጋግጣል። የብልጽግና ፓርቲ የሚያራምደው ብሔራዊ ራዕይ፣ ተቋማትን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በመምራት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ኃይል ለማድረግ ያለመ ነው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለውጥ የአንድ ፖሊሲ ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር የማንሰራራት ምልክት ነው። ከበጀት ጫናነት ወደ ሀብት ፈጣሪነት፣ ከዝግ አሠራር ወደ ግልጽነት የተደረገው ሽግግር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል። የዓለም ባንክ ምስክርነት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም በትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። ይህ ስኬት ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ የኢትዮጵያ ህዳሴና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ከእንግዲህ ምኞት ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ እውነታ መሆኑ አያጠራጥርም።