የአረንጓዴ አሻራ ተግባር ለትዉልድ ተስፋን የመትከል ትልቅ ፕሮጀክት ነዉ
የብልፅግና እሳቤ ስር የሰደደው የሰውን ህይወት በመለወጥ፣ የሀገርን ገጽታ በመቀየር እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ላይ ነው። ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ በተግባር ከሚያሳዩን ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ተራ የአካባቢ ጥበቃ ስራ አይደለም፤ ይህ ስራ የዛሬውን ማህበረሰብ ፍላጎት እያሟላ፣ ለነገው ትውልድ የምትስማማ የበለፀገች ለምለም ሀገር የማስረከብ ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ራዕይ ነዉ።
የዚህ ትልቅ ሀገራዊና አሳታፊ ፕሮጀክት ተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
ይህ ንቅናቄ በዉጤት ያሸበረቀ እንዲሆን ያስቻለው ደሞ ህዝባችን በእድሜ፣ በጾታ፣ በብሄር፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዞ በታላቅ ሀገራዊ ስሜት የሚሳተፍበት ተወዳጅና ተናፋቂ መድረክ ስለ ሆነ ነው። አርንጓዴ አሻራ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከህጻናት እስከ አዛውንት ድረስ ሁሉም ዜጋ እኩል አሻራውን የሚያሳርፍበት በመሆኑ፣ ሀገራዊ አንድነታችንን እና ህብረታችንን በተግባር ያጠናከረ የጋራ ኩራታችን ሆኗል።
በየዓመቱ የምንተክላቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መንግስትና ህዝብ ባደረጉት ተከታታይ እንክብካቤ እና ክትትል፣ የተተከሉት ችግኞች በከፍተኛ ሁኔታ በመፅደቃቸዉ ትናንት የተራቆቱ ተራራዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፣ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል፣የደን ሽፋናችን በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፣ ምንጮች እንደገና መፍለቅ ጀምረዋል፣ የአየር ንብረታችንም እየታደሰ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ ስራችን ከአየር ንብረት ጥበቃ ባለፈ በቀጥታ ከኢኮኖሚ ብልፅግና ጋር ተሳስሯል። ንቅናቄው ከተራ ችግኞች ባለፈ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፍራፍሬ ዛፎችን እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና እና የመሳሰሉትን በማካተቱ፣ ዛሬ ላይ ለብዙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አዲስ የገቢ ምንጭ ፈጥሯል፤ የቤተሰብን የምግብ ዋስትና እያረጋገጠም ይገኛል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያሳየችው ቁርጠኝነት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው ስኬት መላውን ዓለም ያስደነቀ ነው። ሀገራችን በተግባር ያሳየችው ቁርጠኘነት በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚሰሩ ሀገራት ሁሉ እንደ ትልቅ አርአያ እና ተጠቃሽ ተሞክሮ እየቀረበ ይገኛል።
ብልፅግና ዛሬ በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ የሚሆን የተረጋገጠ ህልውና መገንባት ነው።
ለልጆቻችን የተራቆተች፣ የተበከለችና በድርቅ የምትጠቃ ሀገር ሳይሆን፤ አረንጓዴ፣ ምርታማ፣ ለምለም እና በተፈጥሮ ጸጋዋ የተንቆጠቆጠች ውብ ኢትዮጵያን ለማውረስ ከህዝባችን ጋር በቁርጠኝነት እየሰራን ነው።
በአረንጓዴ አሻራ ዘርፍ እስካሁን ያስመዘገብናቸዉን ስኬቶች ይበልጥ በማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥን ሙሉ በሙሉ ለመቋቋም እና የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ታሪካዊ አሻራችንን ለትዉልድ ማኖር እና እንክብካቤውን ባህል በማድረግ የታሪክ ሰሪዉ ትዉልድ አካል እንሁን።