የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ- ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!
የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል። በዞኑ እና በከተማ አስተዳደሩ ቅንጅት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የፓርቲው አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመውጣት የድጋፍ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በዕለቱ ተሳታፊዎቹ “ብልፅግናን መምረጥ ልማትንና አብሮነትን መምረጥ ነው” በሚሉ መፈክሮች የታጀበ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ የብልፅግና ፖርቲ የምርጫ ምልክት የሆነው የ"ስንዴ ነዶ" የሀገሪቱ ራሷን የመቻል ተምሳሌት መሆኑም በጉልህ ታይቷል።
በዚህ ደማቅ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ሳዳት ነሻ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የታዩ ስኬቶችንና የቀጣዩን አምስት ዓመታት ግልጽ ራዕይ ለተሰበሰበው ህዝብ አብራርተዋል።
ክቡር አቶ ሳዳት ነሻ በመልዕክታቸው እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱ በበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም፣ በግብርናውና በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ረገድ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በተለይም በስንዴ ልማት የታየው ስኬት ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆን የቻለችበት ትልቅ ድል መሆኑን አውስተዋል።
አስተባባሪው አክለውም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተቀመጠውን ግብ ሲያብራሩ፣ "ትኩረታችን የጀመርናቸውን የልማት ስራዎች በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ነው" ብለዋል። በሁሉም ዘርፎች የሚታየውን እድገት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ህዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፓርቲው ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም፣ ይህ በምዕራብ ጉጂ ዞን የታየው የድጋፍ ሰልፍ የብልፅግና ጉዞ የማይገታ መሆኑን ያሳየና ለቀጣዩ ምርጫ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑ ተመልክቷል።
ብልፅግናን ይምረጡ!
ምልክታችን የስንዴ ነዶ ነዉ!
#prosperity