Prosperity Party

የሀገር ትንሳኤ በህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይረጋገጣል- ሳምንታዊ መልዕክት

የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ከሞት ወደ ህይወት የሚደረገውን ሽግግር አናስባለን፡፡ ይህ ሽግግር ደግሞ በጥረትና በመስዋዕትነት የታጀበ መሆኑን ልብ እንድንል ያደርገናል፡፡ በዘመናዊ የሀገረ-መንግሥት ብያኔ ሀገር ስጋ በለበሰ እና ነፍስ ባለው ፍጥረት/living organism ይመሰላል፡፡ ማንኛውም ስጋ የለበሰና ነብስ ያለው ፍጡር በህይወት የመኖር እና የመበልፀግ ተፈጥራዊ መሻት አለው፡፡ ሀገርም እንዲሁ ነው፤ ሀገር የአንድን ህዝብ ትልቁ ተቋም እና መሻት መገለጫ ነው፡፡ በሀገርነት የሚገለፀው የህዝብ መሻት ግቡ ትንሳኤነት እና ህልዉነት ነው፡፡ ይህ የትንሳኤነትና የህለዉነት ግብ የሚሳካው ደግሞ በህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከዓርብ ስቅለትዋ ይልቅ የሰንበት ትንሳኤዋ የበዛላት የህዝቦቿ ጥረትና የፈጣሪ ጥበቃ ያልተለያት ድንቅ ሀገር ነች፤ በታሪኳ አያሌ ህማማት እና ስቅለት ቢገጥሟትም መደምደምያው ግን የትንሳኤ ቃልኪዳንዋ እና ትንሳኤዋ ነው፡፡ ስለሆነም ከሚያጋጥማት ስቅለት ወርዳ በትንሳኤ ጎዳናዋ ታደሳ በአዲስ የህይወት ምዕራፍ ትደምቃለች፡፡ 
ፓርቲያችን ብልፅግና ኢትዮጵያንና ትንሳኤን የሚረዳው በእንዲህ ያለ መደመራዊ ዕሳቤ ነው፡፡ መደመር መልካም ክስተት ላይ ብቻ ሳይሆን ዋጋ ያስከፈሉን ጉዳዮችም በአግባቡ ተረድቶ ትላንትን አክሞ ነገን ብሩህ እና ህያው ማድረግ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ትንሳኤያዊ ጎዳና በመጓዝም እስካሁን ሀገርን ከሞት አፋፍ የመለሱና ቀና ያደረጉ አያሌ ለውጦችና ድሎች መቀዳጀት ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዚህ የአሸናፊነትና የትንሳኤ መንፈስ የታጀቡ በርካታ ሀገራዊ ሥራዎች እየተሳለጡ  ይገኛሉ፡፡ የተቋማት ግንባታ፣ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ከተረጂነት መላቀቅ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት፣ የባህር በር ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ሌሎች በጉልህ የሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ያበሰሩና በቀጣይነት እያበሰሩ የሚገኙ ሥራዎችንና ለውጦች መጥቀስ ይቻላል፡፡
በድምቀት እየተሳለጠ የሚገኘው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትንሳኤ እዉን ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እንዲጫወት ሌት ተቀን እየተሰራ ይገኛል፡፡ ጠቅላላ ምርጫው እስከባለፈው ሳምንት ብቻ ከ42 ሚልየን በላይ መራጮች ተመዝግበዉበታል፡፡ ይህም የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ሰፊ ተሳትፎ ሆኖ ተስተዉሏል፡፡ ይህ ሂደት ልክ እንደ የትንሳኤ መንገዱ ቀላልና አልጋ በአልጋ አይደለም፤ ይልቁንም ተስፋና እርግጠኝነት እንደነበሩት ሁሉ ጥርጣሬና ተስፋ መቁረጥም አጋጥመዋል፡፡ ሆኖም ግን ስቅለት በትንሳኤ እንደተደመደመው ሁሉ ጥርጣሬና ተስፋ-መቁረጥንም በእርግጠኝነትና በተስፋ እየተደመደመ ይገኛል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ መላ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸውና በመጪው ተስፋቸው ላይ እምነታቸው ትልቅ መሆኑ ይመሰክራሉ፡፡ ለዚህም ተዘጋጅተን ጀምረን እያጋመስነው ያለነውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእስካሁን አፈጻጸም ህያው ምስክር ነው፡፡ 
ስለሆነም የሀገራችን ትንሳኤ በምልአት እዉን እንዲሆን የጀመርነውን የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት አጠናክረን እንቀጥል፡፡ 
ኢትዮጵያ ህጋዊና ህዝባዊ መንግሥት እንድታስቀጥል እንዲሁም የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል እንድትቀዳጅ ወሳኝ በሆነው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ የዜግነት አሻራችን እናኑር፤ 
በድጋሜ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳቹ፤
ኢትዮጵያ ትመርጣለች፤ የዴሞክራሲ ትንሳኤዋም እዉን ታደርጋለች!

ብልፅግና ፓርቲ

ሚያዝያ 05፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party