ኢትዮጵያ የትስስርና የኢኮኖሚ ኮሪደር ሥርዓት እየዘረጋች ነው- የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ
በሶማሊ ክልል ሲቲ ዞን የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ እና የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በሺኒሌ ከተማ በፋራሕ ዋይስዱሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ይገኝበታል።
በመርሃ ግብሩ ላይ አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፣ የመንገዱ መጠናቀቅ በክልሉ የልማት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ኢትዮጵያ በተግባር የተገነባ የትስስርና የኢኮኖሚ ኮሪደር ሥርዓት እየዘረጋች መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካው በሲቲ ዞንና በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ለሚገኙ የጤና ተቋማት ወሳኝ የሆነውን የሕክምና ኦክስጅን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በ1.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ከሶማሊ ክልል ሺኒሌ ከተማ ጋር የሚያገናኘው የ10.5 ኪሎ ሜትር የድሬዳዋ-ሺኒሌ የአስፓልት መንገድ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በሁለቱ አካባቢዎች መካከል ያለውን የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በማሳለጥ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ታምኖበታል።
በዕለቱ የልማት ፕሮጀክቶቹን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከመደበኛው የምርቃት መርሐ-ግብር ባሻገር በመርማርሳ አስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ በሲቲ ዞን የተከናወኑ ሌሎች የልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል።