አዲሱ "ቮይስ ኦፍ ፕሮስፔሪቲ" (VoP) የእንግሊዝኛ መፅሄት መታተም ጀመረ
የብልጽግና ፓርቲን ራዕይ፣ ቀዳሚ አጀንዳዎች እና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል Voice of Prosperity–VoP (ቮይስ ኦፍ ፕሮስፔሪቲ) የተሰኘ በየወሩ የሚዘጋጅ መፅሄት በፓርቲዉ ዋና ፅ/ቤት የህዝብ እና አለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዲጂታል እና በህትመት አማራጮች የሚዘጋጀዉ ይህ የመረጃ ምንጭ፤ የፓርቲውን ተቋማዊ አሰራር ከማዘመኑም በተጨማሪ ስትራቴጂያዊ የተግባቦት ስራዎችን በማላቅ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተደረገ በሚገኘዉ ጥረት ውስጥ እንደ አንድ ምዕራፍ መታየት የሚችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ህትመቱ ኢትዮጵያ የምታከናዉናቸዉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ለውጦች ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ መድረክ ከመፍጠሩም በላይ በግብዓትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ሃሳቦች እንደሚንሸራሸሩበትም ይጠበቃል።
የመጀመሪያው እትም የተለያዩ ወቅታዊ እና ስትራቴጂያዊ ጭብጦችን የያዘረ ሲሆን፣ የዋና ፅ/ቤት የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል ከሆኑት ከዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ጋር የተደረገ ልዩ ቃለ-መጠይቅንም አካቷል። ዶክተር ቢቂላ በቃለ-መጠይቃቸው ስለ 7ኛው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ እንዲሁም ከ2018 ዓ.ም አንስቶ ዴሞክራሲያዊ ባህልን ለመትከልና ትግበራዉንም ለማፅናት በተደረጉ ሪፎርሞች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ሃገራዊ ምክክር እስካሁን ስለሄደባቸዉ ምዕራፎች እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ስላስመዘገበዉ ቁልፍ ስኬትም ዳስሷል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ባህር በር የማግኘት ስትራቴጂያዊ ጥረት በዝርዝር አቅርቧል ።
የቮይስ ኦፍ ፕሮስፔሪቲ ወደ ስራ መግባት የፓርቲያችንን የተግባቦት አድማስ ከማስፋቱ በተጨማሪ፤ ገንቢ ሃሳቦችንና ውይይቶችን በማበረታታት በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘዉን ሪፎርም እና ተያያዥ ጉዳዮች ለዓለም አቀፍ ታዳሚዎች ለማድረስም ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው ።
መላዉ አንባቢዎችም ሆኑ ፍላጎት ያላቸዉ አካላት በአዲሱ መድረክ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለቀጣይ እትሞች ግብዓት ይሆናሉ የሚሏቸዉን አስተያየቶችና ሃሳባቸዉን እንዲያቀርቡም የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ጥሪ አቅርቧል ።
#prosperity