Prosperity Party

ቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ እና ብልፅግና ፓርቲ ድል መጎናጸፍ አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ሚስተር ቼን ሀይን በፅ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ፓርቲያችን ብልፅግና ለተጎነጸፈው ድል ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የተላከውን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ተቀብለዋል፡፡

ፓርቲው በላከው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት እና በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላምና መረጋጋት፣ ብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና እየተረጋጋጠ እንደሚሄድ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
የምርጫው ውጤትም የኢትዮጵያ ህዝብ ለብልፅግና ፓርቲ ያለውን ልባዊ ድጋፍ የሚያሳይ እና በቀጣይም ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ህዝቦች አስተባብሮ በመምራት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ግብን እውን እንደሚያደርግ ፓርቲው እንደሚያምን ጠቅሷል፡፡
በቀጣይም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ፓርቲ ፕሬዚዳንቶች አማካይነት የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ በትኩረት መስራቱን እንደሚቀጥል እና በልምድ ልውውጥ እርስ በእርስ በመማማር ሂደት መንግስታዊ ልምዶችን በመለዋወጥ ለኢትዮጵያ እና ቻይና እድገት አበክሮ በመስራት በየትኛውም ሁኔታ የማይናወጥ አጋርነትን እየገነባ እንደሚሄድ ፓርቲው ገልጿል፡፡
ከእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በተጨማሪ ክቡር የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ከሆኑት ሚስተር ቼን ሀይ ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የፓርቲ ለፓርቲ፤ የመንግስት ለመንግስት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ክቡር አቶ አደም አንስተዋል፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና ብልፅግና ፓርቲ ሀገር በቀል በሆኑ እሳቤዎች እየተመሩ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን በማፍለቅ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የገለጹት ክቡር አቶ አደም ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ተባብሮ ከመስራትም ባሻገር በተለያየ መስክ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያላቸዉን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቼን ሀይ በበኩላቸው በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ላሉ ድሎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ባለፉት ስድስት ወራትም በርካታ አዳዲስ የቻይና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ በመጥቀስ በማዕድን፤ በአገልግሎት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት፣ በኮንስትራክሽን እንዲሁም በአለምአቀፍ ግንኙነት በጋራ በመስራት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በሁሉም መስኮች የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል እና በጋራ ለመስራት በብልፅግና ፓርቲ እና በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት በመግለጽ ለተደረገላቸው የላቀ አቀባበል ምስጋና በማቅረብ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party