Prosperity Party

ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ዲፕሎማሲ፡ የኢትዮጵያ ስልታዊ ገለልተኝነትና ዓለም አቀፍ ቁመና

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረክ የያዘችው ዲፕሎማሲያዊ አቋም ሉዓላዊነትን የማስከበር ጽናትና ብሔራዊ ጥቅምን ባስቀደመ ስልታዊ ግንኙነት ላይ የተገነባ መሆኑን በተግባር አስመስክራለች። አገራችን በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩ የጎራ ግጭቶችንና ልዩ ልዩ ጫናዎችን በብልሃት በማለፍ፣ ለብሔራዊ ጥቅሟ የሚበጀውን አማራጭ ብቻ የምትመርጥበት የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መሠረታዊ መርሕ በገለልተኝነት ላይ የተመሠረተ እና ከአገራዊ ፍላጎት ጋር የተቃኘ ንቁ ተሳትፎን የተከተለ ነው። ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ከማንኛውም የዓለም ኃይል ጋር የምታደርገው ግንኙነት የሚለካው ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ምን ፋይዳ አለው? በሚለው ስልታዊ መሥፈርት ብቻ ነው።

ይህ ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ አካሄድ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ረገድ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግቧል። አገራችን ከታላላቅ የዓለም ኃይላት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ስልታዊ አጋርነት በማሳደግ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ አገራዊ አቅምን የሚገነቡ ውጤቶችን አግኝታለች። በተለይም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የዲፕሎማሲያዊ ብስለታችን ትልቁ ማሳያ ሲሆን፣ ይህም አገራችን በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት መድረክ ላይ ያላትን ድምፅ ከማሳደጉም በላይ የፋይናንስና የገበያ አማራጮቻችንን በማስፋት ብሔራዊ ጥቅማችንን በላቀ ደረጃ ለማስከበር ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድና በመላው አህጉሪቱ ኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ምሰሶ በመሆን የምታደርገው ጥረት ቀጣናዊ ተጽዕኖዋን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። «የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን» የሚለውን መርሕ በጽናት በመከተል፣ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ ያሳየችው ብቃት ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱ ድምፅ መሆኗን አረጋግጧል። 

ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አገራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም በላይ ለቀጣዩ ትውልድ የማይደፈርና የተከበረ አገር የማስረከብ ስትራቴጂካዊ ጉዞዋን እውን እያደረገው ይገኛል።

#prosperity

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party